ሊቨርፑል ድል ሲቀናው ፒኤስጂ እና ማንችስተር ዩናይትድ ከተጋጣሚዎቻቸው አቻ ተለያይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሊቨርፑል ድል ሲቀናው ፒኤስጂ እና ማንችስተር ዩናይትድ ከተጋጣሚዎቻቸው አቻ ተለያይተዋል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2019 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መርሐ ግብር የአምስተኛ ዙር የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ማምሻውን ተደርገዋል።
በጃን ብሬይድል ስታዲም በተካሄደው ጨዋታ ሊቨርፑል ክለብ ብሩዥን 3 ለ 0 አሸንፏል።
አሌክሳንዳር ኢሳቅ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ፍሎሪያን ዊትዝ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ሊቨርፑል በ12 ነጥብ አምስተኛ፣ ክለብ ብሩዥ በዘጠኝ ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ፒኤስጂ ከሮማ ጋር ሁለት አቻ ተለያይቷል።
በፓርክ ደ ፕሪንስ በተካሄደው ጨዋታ ኢሊያ ዛባርኒዪ እና ኡስማን ዴምቤሌ በፍጹም ቅጣት ምት ለፒኤስጂ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ማሪዮ ሄርሞሶ እና ዶንየር ማለን በፍጹም ቅጣት ምት ለሮማ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
የወቅቱ ሻምፒዮን ፒኤስጂ በ13 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ ሮማ በአምስት ነጥብ 25ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ስፖርቲንግ ሊዝበን እና ማንችስተር ዩናይትድ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
በጆሴ አልቫላድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሉዊስ ሱዋሬዝ የስፖርቲንግን ጎሎች አስቆጥሯል። በተጨማሪም ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል።
ብሩኖ ፈርናንዴዝ በጨዋታ እና ፍጹም ቅጣት ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የዩናይትዱ ዩሪ ቲሊማንስ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ወጥቷል።
ስፖርቲንግ ሊዝበን በ10 ነጥብ 9ኛ እና ዩናይትድ በሰባት ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ባየር ሙኒክ በሊል ያልተጠበቀ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።
አያሴ ኡኤዳ እና የሙኒኩ አሌክሳንደር ፓቭሎቪች በራሱ ላይ ግቦቹን ለሊል አስቆጥረዋል።
ዳዮት ኡፓሜካኖ የባየር ሙኒክን ብቸኛ ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ባየር ሙኒክ በስምንት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል።
የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘገበው ሊል በአራት ነጥብ 29ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አትሌቲኮ ማድሪድ ቫይኪንግን እና ኢንተር ሚላን ስቱትጋርትን በተመሳሳይ 2 ለ 0 አሸንፈዋል።
ፊነርባቼ ሻካታር ዶኔስክን 1 ለ 0 ረትቷል።
ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ ጨዋታዎች ባርሴሎና ሳባህን 4 ለ 1 ፣ ቪያሪያል ስላቪያ ፕራግን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የአምስተኛ ዙር መርሐ ግብር ተጠናቋል።
የስድስተኛ ዙር ጨዋታዎች ህዳር 29 እና 30 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳሉ።