ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የትስስር አጀንዳን በንቃት በመምራት የምትጫወተውን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የትስስር አጀንዳን በንቃት በመምራት የምትጫወተውን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ትስስርን፣ የጋራ ደኅንነትንና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የጋራ አጀንዳዎችን በንቃት በመምራት የምትጫወተውን ሚና አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር አዳም ተስፋዬ ገለጹ።
አምባሳደሩ በአዲስ አበባ በሁለት ቀናት የሚካሄደውን አምስተኛውን የአፍሪካ ቀንድ ውይይት መድረክ በከፈቱበት ወቅት፤ የቀይ ባሕር ደኅንነት ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ እንደሆነና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት የማይነጠል ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት የማግኘት ጥረቷን በሰላማዊ ውይይት፣ በዲፕሎማሲ፣ በዓለም አቀፍ ሕግና በጋራ ተጠቃሚነት መርሆዎች ላይ በመመሥረት እያከናወነች መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የጋራ የሰላም፣ የደኅንነትና የልማት ጥቅሞችን ለማሳካት ስትራቴጂያዊ መተማመንና ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
የድንበር ተሻጋሪ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባሕር ደኅንነት ችግሮች በአንድ ሀገር ጥረት ብቻ መፍታት እንደማይቻል የተናገሩት አምባሳደሩ፤ በቀጣናዊ ትብብርና ውህደት ላይ የተመሠረተ የጋራ ምላሽ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር በትራንስፖርትና በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ኢንቨስት እያደረገች መሆኑንና በኢጋድ፣ በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀፎች ውስጥ በሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲዋሳ አብዲላሂ (ዶ/ር) ተወካይና በውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ግዛቸው አስራት (ዶ/ር)፤ የአፍሪካ ቀንድ ከቀይ ባሕር፣ ከኤደን ባሕረ ሰላጤና ከሕንድ ውቅያኖስ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ ትስስር አንስተው፤ የመተማመን እጥረትና ትብብር ማነስ ሀገራቱ ካላቸው የጋራ ዕድል ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀሙ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆኖም በቀጣናው የሚታዩ ግጭቶች፣ የጸጥታ ችግሮች፣ የኢኮኖሚ ትብብር ማነስ፣ የመተማመን እጥረትና የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ ያሉትን ዕድሎች በሙሉ ለመጠቀም እንቅፋት እንደሆኑ አመልክተዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ውይይት መድረክ ተግባራዊ የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን ለማመንጨትና በቀጣናው የምርምር ተቋማት መካከል የትብብር መረብ ለመገንባት ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኮንራድ አዴናወር ፋውንዴሽን (KAS) የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የደኅንነት ውይይት ፕሮግራም ዳይሬክተር ጃን-ኦሌ ቮስ፤ ዘላቂ የቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ መፍትሔዎች ከውጭ የሚጫኑ ሳይሆን በቀጣናው ሀገራትና ሕዝቦች ተነሳሽነት መመራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ቀንድ የወደፊት አቅጣጫ በቀጣናው ሀገራትና ሕዝቦች የሚወሰን መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀጣናዊ ትብብርን ማሻሻል ያሉትን የአፍሪካ ሕብረትና የኢጋድ ማዕቀፎች በማጠናከር እንጂ በመተካት እንዳልሆነ አብራርተዋል።
በኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲ ስተዲስ (ISS) የምስራቅ አፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተርና በአፍሪካ ህብረት ተወካይ ፖል ሲሞን ሃንዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የጸጥታ ተግዳሮት ለማቃለልና ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር በአገራት መካከል ስትራቴጂካዊ መተማመንና ተግባራዊ ትብብር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የዘንድሮው ውይይት በቀጣናው ስትራቴጂካዊ መተማመንን፣ ቀጣናዊ የውሳኔ ራስን ችሎ የመንቀሳቀስ አቅምን በማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አምስተኛው የአፍሪካ ቀንድ ውይይት መድረክ በጂቡቲ እ.ኤ.አ. በ2022 ከተጀመረ ወዲህ ለአምስተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን፤ ምሁራንን፣ ዲፕሎማቶችንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የቀጣናውን የጋራ ፈተናዎችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ እየመከረ ይገኛል።
የውይይት መድረኩ ከውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ የጸዳ ቀጣናዊ አጀንዳን ማሳደግ፣ በጎረቤት ሀገራት መካከል ስትራቴጂያዊ መተማመንን መገንባትና በፖለቲካዊ ልዩነቶች መካከልም የጋራ ትስስርን ማጠናከር በሚሉ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።