ቀጥታ፡

አፍሪካ በጤናው ዘርፍ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ውስጣዊ አቅሟን አቀናጅታ በትብብር መሥራት አለባት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦አፍሪካ በጤናው ዘርፍ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ውስጣዊ አቅሟን አቀናጅታ በትብብር መሥራት እንዳለባት የአፍሪካ ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች ገለጹ። 

5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ሲሆን፤ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።


 

የሞሪሽየስ የጤናና ደህንነት ሚኒስትር አኒል ኩመር ባቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ ስኬት እያስመዘገቡ ያሉ ሀገራት ተግባር የሚደነቅ ነው። 

አፍሪካ በቀጣይ ዓመታት በጤናው ዘርፍ ከሌሎች አህጉራት ጋር የመወዳደር አቅም እንዳላት አንስተው፤ አህጉሪቱ ከጥገኝነት ተላቃ በባለቤትነትና በግልጽነት ከሠራች ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ እንደምትችል ተናግረዋል።

የሞሪሽየስ መንግሥት ለጤና፣ ለማኅበራዊ ዋስትና እና ለትምህርት በትኩረት እንደሚሠራ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የጤና አገልግሎት ከጽንስ ጀምሮ እስከ ሕልፈት ድረስ በመንግሥት ድጋፍ እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

የስኳር በሽታን ለመከላከል በሆስፒታሎች የተለየ ክፍል መቋቋሙን ጠቅሰው፤ ለልብ፣ ለአረጋውያን፣ ለድንገተኛ እና ለስትሮክ ሕክምናም ልዩ ማዕከላት መኖራቸውን አመልክተዋል።

በጉባኤው በርካታ ተሳታፊዎች መታደማቸው የሚያስደንቅ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለተደረገላቸው መስተንግዶም ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ምስጋና አቅርበዋል።


 

የማዳጋስካር የሕዝብ ጤና ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ዶክተር ኤፍሬም ስቴፋንሰን ራንድሪያናምቢኒና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ መድኃኒቶችን፣ የላቦራቶሪ ግብዓቶችንና የሕክምና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ያሳየችው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ተግባር ለአፍሪካ ሉዓላዊነት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ጠቅሰው፤ በማዳጋስካርና በኢትዮጵያ መካከል የሚኖረው ትብብር የቴክኖሎጂ ዕድገትን ለማፋጠንና የሕክምና መሣሪያዎችን የማምረት አቅም ለመገንባት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ የጤና ሥርዓትን በመምራት ረገድ ለአፍሪካ ምሳሌ እየሆነች መምጣቷን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም