ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ከተልዕኮው ባሻገር የምግብ ፍጆታ ወጪውን በራስ አቅም ለመሸፈን በሀገራዊ የግብርና ልማት ላይ በንቃት እየተሳተፈ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከተልዕኮው ባሻገር የምግብ ፍጆታ ወጪውን በራስ አቅም ለመሸፈን በሀገራዊ የግብርና ልማት ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ገለጹ።

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ አንዶዴ ወረዳ በ16 ሔክታር መሬት ላይ የሚለማ የበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ በ6 ሔክታር መሬት ላይ የበቆሎ ልማት ሥራ አስጀምሯል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ የልማት ሥራውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከተልዕኮው ባሻገር በሀገራዊ የልማት ሥራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።


 

የሕግ ታራሚዎች በዕውቀት፣ በሙያና በሥነ-ምግባር ታንጸው እንዲወጡ የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ይህም የእርምት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ሀገራቸውንና ማኅበረሰባቸውን በታማኝነት የሚያገለግሉ ዜጎች እንዲሆኑ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።

በ16 ሔክታር መሬት ላይ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሕግ ታራሚዎችን የልማት ተነሳሽነት በማሳደግ ሠርቶ የመለወጥ ባህልን እንደሚያዳብር አስረድተዋል።

ልማቱ ኮሚሽኑ የሕግ ታራሚዎችን ከማረምና ከማነጽ ባሻገር በልማት ተነሳሽነቶች ላይ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን፣ ሥራው ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ ከወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።


 

በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ሉባባ ጀማል በበኩላቸው፣ መንግሥት በስንዴ ምርትና ምርታማነት ላይ ሰፋፊ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

ይህንን ምቹ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት ተከታታይነት ያለው የልማት ሥራ ማከናወኑን ጠቁመው፣ በዚህም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ዘንድሮም የአካባቢውን ምቹ የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል ከማረሚያ ቤቱ ፍጆታ ባሻገር ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጭምር የሚተርፍ ምርት ለማምረት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።


 

አካባቢው ለመስኖ ልማት ሥራ ምቹና አምራች መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ አንዶዴ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረሰ ሙላቱ ናቸው።

ጽሕፈት ቤቱ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በ16 ሔክታር መሬት ላይ የሚያለማውን የስንዴ ልማት ለፍሬ ለማብቃት በግብዓትና በሙያዊ ድጋፍ በጋራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም