ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ 270 ኢንተርፕራይዞች በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ሥራ ገብተዋል

ጎንደር፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦በጎንደር ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ 270 ኢንተርፕራይዞች በመንግስት የተደረገላቸውን የቦታና የብድር ድጋፍ ተጠቅመው ወደ ሥራ መግባታቸውን የከተማ አስተዳደሩ ሥራ እና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ። 

በከተማው በአንድ ኢንተርፕራይዝ የተቋቋመ ሚስማር ፋብሪካ በዛሬው እለት ወደሥራ ገብቷል።


 

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉ ደሳለኝ እንደገለጹት፣ በመደመር መንግስት ወጣቱን አደራጅቶ በማሰልጠንና በመደገፍ ወደሥራ የማስገባትና ተጠቃሚነቱን የማረጋገጥ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ ነው።

በዚህም በከተማው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ 270 ኢንተርፕራይዞችን በተለያየ መንገድ በመደገፍ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በኢንተርፕራይዞቹና በተለያዩ የሥራ መስኮችም ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ተናግረዋል።

መምሪያውም ከአበዳሪና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ለኢንተርፕራይዞች ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲሁም የስልጠና፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ በማመቻቸት ፈጥነው ወደሥራ እንዲገቡ ማድረጉን አስረድተዋል።

ወደ ሥራ ከገቡ ኢንተርፕራይዞቸ መካከል ዛሬ ሥራ የጀመረው የሚስማር ፋብሪካ ይገኝበታል ያሉት ኃላፊዋ፣ ለፋብሪካው የኤሌክትሪክ ሀይል፣ የቦታና የገንዘብ ብድር መመቻቸቱ ፈጥኖ ወደ ሥራ እንዲገባ አስችሏል ብለዋል።

ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለኢንተርፕራይዞቹ የገበያ ትስስር የመፍጠር እንዲሁም የማምረት አቅማቸውንና የምርት ጥራትን ማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

የሀብታሙ ጠለለና ጓደኞቻቸው የሚስማር ፋብሪካ የሒሳብ ሠራተኛ አቶ ሀብታሙ ጠለለ ፣ በ2004 ዓ.ም በትንሽ ካፌ ሥራ የጀመረው ድርጅታቸው በየጊዜው እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዙ አንድ ሴት እና አራት ወንዶችን አቅፎ መያዙን ገልጸው፣ በከተማ አስተዳደሩ በመስሪያ ቦታ እና ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሊዝ ፋይናንሲንግ ብድር ድጋፍ ሚስማር ፋብሪካ ለመገንባት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

​ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 50 ኩንታል የተለያዩ ሚስማሮችን የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ለ15 ተጨማሪ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

በፋብሪካው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ኃይሉ እሸቴ በበኩሉ፣ በሰለጠነበት የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለብዙ ዓመታት ሥራ አጥቶ መቆየቱን አስታውሷል።


 

በአሁኑ ወቅት በፋብሪካው ተቀጥሮ በሚያገኘው ገቢ ራሱን ከማስተዳደር ባለፈ ቁጠባውን በማጠናከር ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ሕልም እንዳለው ተናግሯል።

ሌላኛው የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ክብሩ ጸጋዬ በበኩሉ፣ በፋብሪካው በመካኒክነት ሙያ ተቀጥሮ የተበላሹ ማሽኖችን የማስተካከልና ሠራተኞችን የማሰልጠን ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም