ቀጥታ፡

የታራሚን ሰብዓዊ መብት ከመጠበቅ ባሻገር በልማት መስኮች ንቁ ተሳትፎ እየተደረገ ነው 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የታራሚን ሰብዓዊ መብት በመጠበቅ ተስፋን ከማለምለም ባሻገር በልማት መስኮች ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ገለጹ። 

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የ2019 ዓ.ም የ16 ቀናት ፆታ ተኮር ጥቃት የመከላከል ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ተጀምሯል።

ንቅናቄውን የኮሚሽኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮችና በዘርፉ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስጀምረውታል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ በዚሁ ወቅት፤ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ወንጀል ነው ብለዋል።

ሴቶች በማንነታቸው፣ በትምህርት ደረጃቸው፣ በኢኮኖሚ አቅማቸውና በማኅበራዊ ተሳትፏቸው የጥቃት ሰለባ መሆን እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች በማረሚያ ተቋማት የሚገኙ ሴቶች ሰብዓዊ ክብራቸውና መሰረታዊ ፍላጎታቸውን በመጠበቅ የወደፊት ተስፋቸውን በመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የ16 ቀናት ንቅናቄውም የአጋር አካላትን ትብብር በማጠናከር ለሴት ታራሚዎች መማር፣ አዳዲስ ክህሎትን የማዳበርና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ዕድል እንደሚፈጥር አንስተዋል።


 

በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር መብራት መኮንን በበኩላቸው፤ ንቅናቄው የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

በሕግ ጥላ ስር ለሚገኙ ሴቶች የሚደረጉ ልዩ ድጋፎችም የፍትሕ እኩል ተደራሽነትና መልሶ ማቋቋምን በማበረታታት ለቀጣይ የሕይወት ምዕራፋቸው መሰረት የሚጥል መሆኑን አስረድተዋል።

በተያያዘ ዜናም የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ አንዶዴ ወረዳ በ16 ሔክታር መሬት የሚለማን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ንቅናቄ አስጀምሯል።


 

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ በዚሁ ወቅትም፤ ሕግ ታራሚዎች በእርምት ቆይታቸው በበጎ ስነ ምግባር በመታነጽ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በ16 ሔክታር መሬት ላይ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም የሕግ ታራሚዎችን የልማት ተነሳሽነት በማሳደግ ሰርቶ የመለወጥ ባህልን እንደሚያሳድግ አስረድተዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱም ኮሚሽኑ የሕግ ታራሚዎችን ከማረምና ከማነጽ ባሻገር በልማት ተነሳሽነቶች ላይ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን እንደሚያመላክት አስረድተዋል።

በ16 ሔክታር መሬት ላይ የሚለማው የመስኖ ስንዴም ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ ከወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ጋር በቅንጅት የሚሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም