ቀጥታ፡

14 ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን አቀባበል ተደረገለት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16 /2019 (ኢዜአ)፦ በኔፓል በተካሄደው የእስያ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ላይ በተጋባዥነት ተሳትፎ ከ10 ሀገራት 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ አቀባበል ተደርጎለታል።

ቡድኑ በግል፣ በቡድን ፋይት እንዲሁም በፓተርን ውድድሮች ላይ ባደረገው ተሳትፎ 4 ወርቅ፣ 3 ብር እና 7 ነሐስ በአጠቃላይ 14 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችሏል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ መንግስቱ ሳህሌ ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ አቀባበል በማድረግ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።




አቶ መንግስቱ ይህ ታሪካዊ ውጤት እንዲመዘገብ ከፍተኛ ተጋድሎ ላደረጉ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች፣ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አመራሮች እንዲሁም ድጋፍ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ ድል ከስፖርታዊ ሜዳሊያ ባለፈ ለሀገራዊ አንድነት፣ ለዲፕሎማሲ እና ለወጣቶች ግንባታ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በኔፓል መድረክ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ መውለብለቡና ብሔራዊ መዝሙር መዘመሩ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጋራ ኩራት እንዲሰማቸው በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን ያጠናክራል።

በኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው የረጅም ርቀት ሩጫዎች ባሻገር በሌሎች የስፖርት ዘርፎችም ተወዳዳሪና አሸናፊ መሆኗን ማሳየቱ የዜጎችን በራስ የመተማመን መንፈስ እና የይቻላል ስነ-ልቦና ይገነባል።

በተጋባዥነት በተደረገ ውድድር ላይ ተገኝቶ ማሸነፍም ኢትዮጵያ ከእስያ ሀገራት በተለይም ከኔፓል ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ እና የባህል ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም