ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ አሳድገዋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጋቸውን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሁንዴ ከበደ ገለጹ።

በመደመር እሳቤ የሚመራው መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባከናወናቸው ግዙፍ የቱሪዝምና የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ አዲስና ዘመናዊ የከተማ ገጽታን ተላብሳለች። 

ይህ የተቀናጀ የልማት አቅጣጫ መዲናዋን ለነዋሪዎቿ እጅግ ምቹ ከማድረግ ባለፈ፣ የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ቀዳሚ መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል። 


 

በተለይም በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ኢኒሼቲቮች አማካኝነት ለዘመናት ተረስተውና አቧራ ለብሰው የቆዩ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ተገልጠው እንዲለሙ ተደርጓል። 

በዚህም ሂደት በከተማዋ የተገነቡ ዘመናዊ ፓርኮች፣ አምፊ ቲያትሮችና ማራኪ የመዝናኛ ስፍራዎች የከተማዋን ውበት በከፍተኛ ደረጃ ቀይረውታል። 

የመደመር መንግሥት የሀገርን እምቅ አቅም አቀናጅቶ የመጠቀም ስትራቴጂ፣ እነዚህን ድብቅ ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጠቀሜታና የሥራ ዕድል መቀየር ችሏል። 

እነዚህ ሁለንተናዊ የልማት ውጤቶች የአዲስ አበባን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ከፍ በማድረግ፣ ዘላቂ ብልፅግናን የማረጋገጥ ጉዞን በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሁንዴ ከበደ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ ሚና እንዲጫወት በርካታ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።


 

በከተማዋ የተገነቡ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችና የተገነቡ መሠረተ ልማቶች የቆዩ ጸጋዎችን ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር ማስቻላቸውን አብራርተዋል።

ወደ መዲናዋ የሚመጡ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ቁጥር ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በታች አሁን ላይ በዓመት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የሀገር ውስጥ የቱሪስት ፍሰቱ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በ2018 በጀት ዓመት ወደ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን አስታውቀዋል።

አዲስ አበባ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን ይበልጥ እያጠናከረች መምጣቷን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ221 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት ማስተናገዷን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ጉባኤዎችን በስኬት ማካሄድ የሚያስችላትን አቅም መገንባቷንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም