ቀጥታ፡

ፖላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢንቨስትመንት አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ፖላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ተሳትፎና የኢንቨስትመንት አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የፖላንድ ኤምባሲ የሚሲዮን ዋና ኃላፊ ኢሎና ኮርቹት ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያና ፖላንድ ረዥም ዘመን የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ፣ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው ከ1930ዎቹ ጀምሮ ነው። 

በኢትዮጵያ የፖላንድ ኤምባሲ የሚሲዮን ዋና ኃላፊ ኢሎና ኮርቹት እንደገለጹት፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየሠራች ነው፡፡

ሁለቱ ሀገራት ባሳለፍነው ዓመት የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክሮችና የጋራ ትብብር ማካሄዳቸውን ጠቅሰው ይህም ለጋራ ፕሮጀክቶች መሪ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል። 

በሀገር ውስጥ፣ በቀጣናዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለው የጋራ አቋም ለሁለቱ ሀገራት ትብብር ዋነኛ መሠረት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማትና በሪፎርም ሥራዎች ረገድ እያከናወነች ያለውን እንቅስቃሴ ፖላንድ በቅርበት ስትከታተል መቆየቷን አስታውቀዋል።  

ይህም የአሠራር ደንቦችን ማሻሻሉንና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አድንቀው፣ ፖላንድም በዚህ ሂደት የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከትና የተፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል። 

ፖላንድ ውጤታማ የኢኮኖሚ ሽግግር ማድረጓን ጠቁመው ሀገራቸው ኢትዮጵያ በማካሄድ ላይ ለምትገኘው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬታማነት ያላትን ልምድ ለማጋራት ዝግጁ እንደሆነች አስታውቀዋል።  

ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኙም ሆነ ከ15 ዓመታት በኋላ ተመልሰው ሲመጡ፣ ሀገሪቱ በታሪክና በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች መሆኗን መመልከታቸውን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊና የተፈጥሮ የመስህብ ሥፍራዎች ያሏት በመሆኑ፣ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ሰፊ አቅም እንዳላት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም