ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የቀጣናውን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ያጠናክራል -ምሁራን

አሶሳ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጣናው ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

የባህር በር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነቷን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለማስከበር እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ጥያቄው የዜጎች ህልውና ሆኖ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ የባህበር ባለቤትነት በቀጣናው የንግድ ትስስርን ለማጠናከርና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠን እንዲሁም ለዘላቂ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የማይተካ ሚና አለው።

በዚህም በሴራ ያጣችውን የባህር በሯን እንድታገኝ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እያደረጉ ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መሪ ስራ አስፈጻሚ፣ መምህርና ተመራማሪ ጌታቸው ወዲሻ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የራሷ የነበረውን የባህር በር በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት የጀመረችው የዲፕሎማሲ ስራ የሚበረታታ ነው።


 

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ መረጋገጥ ከሯሷ በተጨማሪ የቀጣናውን ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

የባህር በር አንድን ሀገር በኢኮኖሚ ጠንካራ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

በቀይ ባህር ቀጣና የሚገኙ ሀገራት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ተባባሪ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ትብብሩ የቀጣናው ሀገራትን በጠንካራ ኢኮኖሚ መሠረት ላይ የሚያስቀምጥ በመሆኑ የውጪ ጫናዎችን ለመቋቋም በትብብር ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲን በመከተል ባህር በርን ለጋራ ተጠቃሚነት ማዋል ይገባል ብለዋል።


 

በዩኒቨርስቲው የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ንጋቱ አምቢሳ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል የባህር በር ማግኘት አንዱ መፍትሔ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ይበልጥ በማጠናከር የባህር በርን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንድታገኝ አሁንም የተጀመረውን ጥረት ማስቀጠል የትውልዱ ግዴታ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የባህር በር የወጪ እና ገቢ ንግድን በማመጣጠን ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም