ቀጥታ፡

በዓሉ የሕዝቦችን እኩልነት፣ብዝኃነትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያጸና ታላቅ መድረክ ነው

ባህር ዳር፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሕዝቦችን እኩልነት፣ ባህላዊ ብዝኃነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጸና ታላቅ መድረክ መሆኑ ተገለጸ።

"በብዝሃነት የደመቀች፣ በምክክር የጸናች፣ ስልጡን ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ የሚከበረውን 21ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በማስመልከት በባህር ዳር ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አዲሴ ትርፌ እንደገለጹት፣  የቀኑ መከበር ሕዝቦች በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያደርግ ነው።

በዓሉ የሕዝቦችን እኩልነት፣ ባህላዊ ብዝኃነትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያጸና ታላቅ ብሔራዊ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዓሉ በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት በማጉላት የሕዝቦችን ወንድማማችነትና አብሮነት እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።  

ባህር ዳር ከተማ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ተከባብረው የሚኖሩባት የንግድና የቱሪዝም ማዕከል የመሆኗን አስታውሰው፣ የቀኑ መከበር በከተማዋ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።


 

ባህር ዳር ከተማ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን የጠቀሱት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ናቸው።

በዓሉ ሲከበር በሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ በወል ትርክትና በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና በማሳደግ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

የቀኑ መከበር ብዝሃነትን ያከበረ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት ያስችላል ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ ይህም ጠንካራ ሀገርንና ሰላምን ለማጽናት ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

የዘንድሮ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በጅማ ከተማ በመጪው ሕዳር 29 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚከበር መገለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም