ቀጥታ፡

በክልሉ የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ሽፋንን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል 

ሆሳዕና፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ሽፋንን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ።

የክልሉ ጤና ቢሮ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በሆሳዕና ከተማ እየመከረ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በመደመር መንግስት የጤና ልማት ሥራዎች አጠናክሮ በመቀጠል የህዝብን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የጤና መድህን አገልግሎት የጤና ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፣ ፕሮግራሙ ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት በተሻለ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በተለይ የጤና መድህን አባላትና ከፍለው መታከም የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተሻለ ሁኔታ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የአገልግሎቱን ተደራሽነት በማስፋት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ለዚህም በፕሮግራሙ አፈጻጸም የሚስተዋሉ ልዩነቶችን ማጠበብ፣ አዳዲስ የጤና መድህን አባላትን ማፍራት እና ከህብረተሰቡ የሚሰበሰበውን ገንዘብ በወቅቱ ገቢ ማድረግ ላይ ቅድሚያ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የሕክምና አገልግሎት የማያገኝ አንድም ዜጋ እንዳይኖር በማድረግ የማህበረሰብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።


 

አቅም የሌላቸው ዜጎች በጤና መድህን አገልግሎት በኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጀመረው ጥረት በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተያዘው በበጀት ዓመት ከ1 ሚሊዮን 100 ሺህ በላይ አባላትን ተጠቃሚ በማድረግ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አመልክተዋል።

ለዚህም ስኬታማነት የአባላትን ቁጥር መጨመር፣ መዋጮን በተገቢው መሰብሰብ፣ የገቢ አማራጮችን መፍጠርና የመክፈል አቅምን ተመጣጣኝ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና ተደራሽነትን ለማሳደግ በቅንጅት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም