የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ የቴክኖሎጂ ክህሎትና ብቃታችንን እንድናሳድግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል - ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ የቴክኖሎጂ ክህሎትና ብቃታችንን እንድናሳድግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል - ተማሪዎች
ወልቂጤ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ ማህበረሰባዊ ችግሮችን የሚፈቱ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያበለጽጉና የቴክኖሎጂ ክህሎትና ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና በከተማው የሚገኙ ተማሪዎች ገለጹ።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ እና እንደ 5 ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስ ያሉ ሀገራዊ የዲጂታል ክህሎት ማሳደጊያ ፕሮግራሞች፣ ወጣቶችና ተማሪዎች ዘመናዊ የዲጂታል መሳሪያዎችን በመጠቀም የአካባቢያቸውን ችግሮች የሚፈቱ መፍትሔዎችን እንዲያመነጩ ዓላማ አድርገዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና በከተማው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ይህንን እድል በመጠቀም የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ማጎልበታቸው፣ ከማዕከላዊ ከተሞች ባሻገር በክልልና በዞን ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ዲጂታል ስነ-ምህዳር እየገቡ መሆኑን ያመላክታል።
በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዲጂታል ግብዓቶችና የፈጠራ ማዕከላትን በማስፋፋት ተማሪዎች ንድፈ ሀሳብን ወደ ተግባራዊ የፈጠራ ሥራ እንዲቀይሩ መደገፋቸው፣ ለተማሪዎቹ የክህሎት እድገት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ እና ለማኅበረሰቡ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማቅረብ ወሳኝ መሰረት ሆኗል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተማሪ አዲል ከድር እንዳለው፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን የተለያዩ የኮዲንግ እና የስታርት አፕ ስልጠናዎችን ወስዷል።
ይህም የቴክኖሎጂ ዕውቀቱን በተግባር እንዲያውል እድል መፍጠሩን ጠቅሶ፤ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ችግር ፈቺ የሆኑ ሶስት መተግበሪያዎችን ማበልጸጉን ገልጿል።
ከእነዚህም መካከል በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መዝግቦ የሚይዝና መረጃ የሚሰጥ፣ ተማሪዎች የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶችና የገበያ ሁኔታ የሚያመላክት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አገልግሎት የሚያዘምን የመረጃ አያያዝ መተግበሪያ ይገኙበታል ብሏል።
በዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ እንቁ ቅርስ በበኩሏ፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ ሴት ተማሪዎች በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎና በራስ መተማመን እንዳሳደገላቸው ተናግራለች።
በቀሰመችው የቴክኖሎጂ ክህሎት በመታገዝ በጉዞ ላይ የሚያጋጥሙ ጥቃቶችን አስቀድሞ የሚጠቁምና ጥቃት ከተፈጸመም መረጃዎችን መዝግቦ የሚይዝ መተግበሪያ ማዘጋጀቷን ገልጻለች።
በተጨማሪም ነፍሰ ጡር እናቶች የእርግዝና ክትትላቸውን የሚያቀላጥፉበት መተግበሪያ ከጓደኞቿ ጋር ሆነው ማበልፀጋቸውን እንዲሁ አመልክታለች።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ አካል የሆነው "ኢትዮ-ኮደርስ" ስልጠና ራሱን በቴክኖሎጂ እንዲያንጽ ትልቅ ዕድል እንደፈጠረለት የገለጸው ደግሞ በወልቂጤ ከተማ የያበሩስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዮናታን ሙሉቀን ነው።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናን ሙሉ በሙሉ በመውሰድ በራሱ ጥረት ሀገር በቀል መተግበሪያዎችን ማበልጸግ መጀመሩን ጠቁሞ፤በተለይም በጤናው ዘርፍ ለማህበረሰቡ ጠቃሚ ምክሮችንና መረጃዎችን የሚሰጥ መተግበሪያ ማዘጋጀቱን አስረድቷል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዲፓርትመት ዳይሬክተር መምህር ጀማል አህመድ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በራስ አቅምና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ማተኮር ለሚፈልጉ ተማሪዎች የተሟላ መሠረተ ልማት አመቻችቶ እየሰራ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግና በከተማው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የወልቂጤ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሐምዱ ካሚል በበኩላቸው፤ ባለፉት አራት ወራት ብቻ ለ1 ሺህ 750 ተማሪዎች የዲጂታል ክህሎት ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከመደበኛ ትምህርታቸው ባለፈ በሳይበር ደህንነት፣ በመተግበሪያዎች ማበልፀግ፣ በስታርት አፕና ሌሎች የዲጂታል ክህሎቶችን ለማሳደግ ማስቻሉን አውስተዋል።
የጉራጌ ዞን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ዓብይ ወልደሰንበትም፤ በዞኑ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦና ተነሳሽነት ያላቸው ዜጎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ድጋፍና ማበረታቻ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስፋፋት የሀገርን ዕድገት ለማፋጠን ወሳኝ ሚና እያበረከተ እንደሆነም ገልጸዋል።