በክልሉ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ረገድ ውጤት እየተመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ረገድ ውጤት እየተመዘገበ ነው
ቦንጋ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጠንካራ ትግል ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ገለፀ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አይበራ ለአዜአ እንደገለጹት፤ ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እንቅፋት የሆነውን ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በክልሉ ጠንካራ ትግል እየተደረገ ነው።
ሙስናን የማይሸከም ማህበረሰብን ለመገንባትም በመልካም ስነ-ምግባር፣ በሙስና ወንጀልና መከላከያ መንገዶቹ ላይ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።
ለሙስና አጋላጭ የሆኑ ሁኔታዎችን በጥናት ለይቶ ቀድሞ ከመከላከል በተጨማሪ የተሿሚዎች እና የመንግስት ሠራተኞችን ሀብት በመመዝገብ የግልጸኝነትና ተጠያቂነት አሠራርን የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በሩብ ዓመቱ ኮሚሽኑ 270 የሙስና ጥቆማዎችን በተለያዩ ዘዴዎች እንደተቀበለ ተናግረዋል።
የተቀበላቸውን ጥቆማዎች መሰረት በማድረግ በ26ቱ ላይ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ የተከናወነ ሲሆን 84 ጥቆማዎች ለፍትህ አካላት ተላልፈው መሰጠታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 94ቱ በምክር አገልግሎትና በአስተዳደራዊ እርምጃ እንዲፈቱ መደረጉን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸው፣ ቀሪዎቹ ጥቆማዎች በሂደት ለይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተደረገው የተቀናጀ ጥረት ከ33 ሚሊዮን 755 ሺህ ብር በላይ የመንግስትና የሕዝብ ሀብትን ከምዝበራ ለማዳንና ለማስመለስ መቻሉን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ28 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ የሚሆነው በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ የዳነ መሆኑንም አመልክተዋል።
በተጨማሪም 13 ሺህ 123 ካሬ ሜትር የከተማ እና ግማሽ ሄክታር የገጠር መሬት ማስመለስ መቻሉን ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ ተናግረዋል።
በክልሉ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት የ170 ሥራ ሃላፊዎችና የመንግስት ሠራተኞችን ሀብት በመመዝገብ የመረጃ ትክክለኛነትን የማጣራት እንዲሁም ተጠያቂነትና ግልጽነትን የማስፈን ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።