የ2026 የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች የመጨረሻ አምስት እጩዎች ይፋ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
የ2026 የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች የመጨረሻ አምስት እጩዎች ይፋ ሆኑ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16 /2019 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የ2026 የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ወንድ እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማት የመጨረሻ አምስት እጩዎችን ዛሬ በይፋ አሳውቋል።
ካፍ ከመጀመሪያዎቹ አስር እጩዎች መካከል በክለብና በብሔራዊ ቡድን ባሳዩት የላቀ ብቃት ተለይተው የቀረቡት ተጫዋቾች አሽራፍ ሃኪሚ፣ ብራሂም ዲያዝ፣ እስማኤል ሳይባሪ፣ ፓፔ ጉዬ እና ሳዲዮ ማኔ መሆናቸውን ገልጿል።
የመጨረሻዎቹ አምስት እጩዎች ዝርዝር ሶስት የሞሮኮ እና ሁለት የሴኔጋል ኮከብ ተጫዋቾች የያዘ ነው።
ካፍ ባወጣው መሰረት የ2026 የካፍ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ረቡዕ ኅዳር 23 ቀን 2019 ዓ.ም በናይጄሪያ ሌጎስ ይካሄዳል።
ሌጎስ ይህንን ታላቅ የአፍሪካ እግር ኳስ የሽልማት መድረክ ስታስተናግድ ከእ.ኤ.አ 2014 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በዚሁ የሽልማት ምሽት ከምርጥ ተጫዋች ባሻገር የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ፣ ምርጥ አሰልጣኝ፣ ምርጥ ወጣት ተጫዋች፣ ምርጥ ክለብ እና ምርጥ ብሔራዊ ቡድን አሸናፊዎች ይታወቃሉ።
የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮኗ ሴኔጋል፣ እስከ ዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የደረሰችው ሞሮኮ እና አስገራሚ ጉዞ ያደረገችው ኬፕ ቨርዴ ለዓመቱ ምርጥ ብሔራዊ ቡድን ሽልማት በመጨረሻ እጩነት ቀርበዋል።
የወቅቱ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ወንድ እግር ኳስ ተጫዋች አሸናፊ ሞሮኳዊው የፒኤስጂ ተከላካይ አሽራፍ ሃኪሚ ነው።