ቀጥታ፡

የትምህርት ዘርፍ የለውጥ ሥራዎች ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ በመፍጠር የሀገርን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ ናቸው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ቦንጋ፣ ህዳር 16/2019 (ኢዜአ)፦ የትምህርት ዘርፍ የለውጥ ሥራዎች ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ በመፍጠር የሀገርን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ "በትምህርት የጸናች ሀገር፤ በጽናት የቆመ ትውልድ" በሚል መሪ ቃል 3ኛውን የትምህርት ጉባኤ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፤ በትምህርት ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ በመፍጠር የሀገርን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ ናቸው።

እንደ ሀገር ለትምህርት ዘርፍ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆን፣ ግብረ ገብነት ያለውና በቴክኖሎጂ የበቃ ትውልድ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ከተለመደው አሰራር በመውጣት የተለየ እይታን መከተልና መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት "በትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ 86 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት በመሰብሰብ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን የመገንባትና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ በትኩረት መከናወኑን ገልጸዋል።

በሁሉም ወረዳዎች አንድ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት እንዲኖር በማቀድ በትምህርት ሚኒስቴርና በክልሎች ትብብር 1 ሺህ 452 ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ሚኒስትሩ አክለዋል።

በተጨማሪም በሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኮምፒውተር ላቦራቶሪ የማደራጀትና በፋይበር ኦፕቲክስ የማስተሳሰር ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በክልሉ በትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በተለይ ለተማሪዎች ውጤታማነት አበክሮ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው በክልሉ የትምህርት ጥራትንና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የአመራሩን፣ የመምህራንን፣ የወላጆችንና የማህበረሰቡን ሚና በማቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።


በተለይ "በትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ ህብረተሰቡን የትምህርት ልማት ባለቤት በማድረግ በተሰሩ ሥራዎች የተገኘውን አበረታች ውጤት ለማስቀጠል በትጋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የትምህርት ፋይናንስ ሥርዓቱን በግልጽነትና በተጠያቂነት መምራትና ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ሥራም በትኩረት እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ዘንድሮ የመማር ማስተማር ሥራውን በማጠናከር የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አዝመራ አንደሞ በበኩላቸው፤ "በትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ የተገነቡ ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂ ማደራጀት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።


መምህራን ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች እየተሰጣቸው መሆኑንም ተናግረዋል።


የተማሪዎች ምገባ፣ የጎልማሶች ትምህርት፣ የተማሪዎችን የትምህርት ተነሳሽነት መጨመር እና የመምህራንን አቅም ማጎልበት ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው የትምህርት ጉባኤ ላይ የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች እንዲሁም የትምህርት ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም