ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቁርጠኛ ናት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በቀጣናዊ ትብብር፣ በዲፕሎማሲና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመሥርታ በትጋት እየሠራች መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር አዳም ተስፋዬ ገለጹ።

አምስተኛውን የአፍሪካ ቀንድ የውይይት መድረክ ‘’ ቀጣናዊነትን በአፍሪካ ቀንድ እንደገና መቃኘት፤ ስትራቴጂካዊ መተማመንን፣ ቀጣናዊ ባለቤትነትን እና በትብብር ላይ የተመሠረተ መደጋገፍን መገንባት ‘’  በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡ 

በዚሁ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር አዳም ተስፋዬ እንደገለጹት፣ የቀጣናው ሀገራት የጋራ የሰላምና የልማት ፍላጎቶቻቸውን እውን ለማድረግ ስትራቴጂካዊ መተማመንንና የትብብር መንፈስን ማጠናከር ይገባቸዋል። 

የቀጣናውን አንገብጋቢ የጂኦፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ለመዳሰስ ምሁራንን፣ ዲፕሎማቶችንና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት አሰባስቧል።

የአፍሪካ ቀንድ በስትራቴጂካዊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ፣ በኢኮኖሚ አቅሙ እንዲሁም በታሪካዊና ማኅበራዊ ትስስሩ ከፍተኛ ዕምቅ ሀብት ያለው ቀጣና መሆኑን ጠቁመዋል። 

ድንበር ተሻጋሪና የባሕር ላይ የደህንነት ሥጋቶችን በአንድ ሀገር የተናጠል ጥረት ብቻ መቅረፍ እንደማይቻል አስገንዝበው ለዘላቂ መረጋጋት ቀጣናዊ ትብብርና ውህደት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ይህንኑ የትብብር መርህ በተግባር ለማሳየት በድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርትና የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት እያካሄደች መሆኗን ጠቅሰዋል። 

አክለውም በኢጋድ (IGAD)፣ በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀፎች ውስጥ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ንቁ የዲፕሎማሲ ተሳትፎ እያደረገች እንደምትገኝ አብራርተዋል።

የቀይ ባሕር ደህንነት ከቀጣናው አጠቃላይ መረጋጋት ጋር በጥብቅ የተቆራኘና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት የማይነጠል ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው የባሕር ጉዳዮች አስተዳደር ላይ ገንቢና ኃላፊነት የተሞላበት ሚና መጫወቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። 

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት በሰላማዊ ውይይት፣ በዲፕሎማሲ፣ በዓለም አቀፍ ሕግና በጋራ ተጠቃሚነት መርሆች ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስገንዝበዋል። 

በእነዚህ መርሆች የሚመሩ የትብብር ስምምነቶችም በአፍሪካ ቀንድ የጋራ ብልፅግናን ለማምጣት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም