የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከችግኝ ተከላ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከችግኝ ተከላ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን እያስገኘ ነው
ወላይታ፤ ሶዶ ኅዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከችግኝ ተከላ ባሻገር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ መድረክ ላይ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ማድረጉን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስታወቁ።
የመደመር መንግስት ባለፉት አመታት ባከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎችና የደረቁ ምንጮች መልሰው እንዲያገግሙ፣ የግበርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከማድረጉ በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን እያስገኘ ነው።
መርሃግብሩ አገሪቷን አረንጓዴ ገጽታ በማላበስ፣ የገጠሩን ማህበረሰብ ህይወት በማሻሻልና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም መልክአ ምድር በመገንባት የተሳካ ውጤት አስገኝቷል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተከናወኑ ተግባራት የተገኘው ውጤትንም ተከትሎ ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ32) እንድታዘጋጅ እንድል ማግኘቷን ለአብነት አንስተዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደገለጹት አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት በማሳደግና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ታሪካዊ እመርታ አምጥቷል፡፡
በዩኒቨርሲቲዉ ግብርና ኮሌጅ የሆርቲካልቸር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አብርሃም ሹምቡሎ (ዶ/ር) አረንጓዴ አሻራ የሕይወት፣ የአየር ፀባይና የምግብ ዋስትና መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ እንሰት፣ ቡና እና አቮካዶ ያሉ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በመርሃ ግብሩ መካተታቸው የዜጎችን ገቢ ለማሳደግ እና ድርቅን ለመቋቋም እያገዙ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ችግኞችን በማበርከት በዓለም አቀፍ መድረክ ትልቅ ተሞክሮ የሚሆን ተግባር መፈጸሟም የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ይህንን ተሞክሮ ለማስፋት ዩኒቨርሲቲዉ የአረንጎዴ አሻራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከፍቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዉ እሳቸዉም የበኩላቸዉን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲዉ የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አለፉ ጭናሾ (ዶ/ር) በበኩላቸዉ የአረንጎዴ አሻራ መርሐ-ግብር የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመግታት ትልቅ ሚና እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።
በመርሃ ግብሩ የተካተቱት የጥምር ደን ዘዴዎች የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ የውሃ ብክለትን በማስቀረት እና ለእንስሳት መኖ በመሆን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንደሚሰጡም ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የካርቦን ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆንና በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ተሰሚነት እንድታገኝ አስችሏታል ነዉ ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ሕዝብን በስፋት በማነቃነቅ ባለፉት ዓመታት በተናጠል ከተሰሩ ሥራዎች እጅግ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲዉ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ መምህርና የአረንጓዴ አሻራ አስተባባሪ ነቢዩ ማሴቦ(ዶ/ር) ናቸዉ።
ግብርና ምርታማ የሚሆነው የተፈጥሮ ሀብት ሲጠበቅ ብቻ መሆኑን ጠቁመው፣ በአረንጎዴ አሻራ ሥራዎች የተራቆቱ መሬቶች አገግመዉ ምርታማ መሆናቸው ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲውም ችግኝ ከመትከል ባለፈ የተተከሉትን የመንከባከብ እና ቀጣይነታቸውን የመከታተል ኃላፊነቱን በትኩረት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሀገር አልፋ ለዓለም ምሳሌ የሆነችበትን የአረንጎዴ አሻራ መርሃ ግብር ቀጣይነት ለማረጋገጥ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።