ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነት ለኢኮኖሚያዊ እድገትና ለቀጣናዊ ትብብር መሰረት ነው - ምሁራን

ጅማ፤ ህዳር 16/2019 (ኢዜአ)፦ ከቀይ ባሕርና ከዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ጋር ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ትስስር ያላት ኢትዮጵያ፣ አስተማማኝ የባሕር በር ተደራሽነት ማረጋገጥ ለሀገራዊ ዕድገቷና ለቀጣናዊ ትብብር የማይተካ ሚና እንዳለው ምሁራን አስታወቁ።

በቀይ ባሕር የንግድና የባሕር ኃይል እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ተዋናይ ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት የራሷ የባሕር በር ሳይኖራት መቆየቷ በወጪና ገቢ ንግዷ እንዲሁም በሎጂስቲክስ ወጪዎቿ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲፈጥር ቆይቷል። 

የባህር በር አልባ መሆን ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ላላትና በፍጥነት እያደገ ለሚገኘው ኢኮኖሚዋ ስትራቴጂካዊ ስጋት በመሆኑ፣ ሀገሪቱ በሰጥቶ መቀበል እና በጋራ ልማት መርህ ላይ የተመሠረተ አማራጭ የባሕር በር ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሁለንተናዊ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች። 

ይህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሠረተ ልማትና በንግድ በማስተሳሰር የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደትንና የጋራ ብልጽግናን ለማፋጠን ያለመ ነው።

በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን እንዳሉት፤ ከቀይ ባሕርና ከዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ጋር ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ትስስር ያላት ኢትዮጵያ፣ አስተማማኝ የባሕር በር ተደራሽነት ማግኘቷ ለሀገራዊ ዕድገቷና ለቀጣናዊ ትብብር የማይተካ ሚና አለው።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ዩናስ ሰይፉ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕርና ከኤደን ባሕረ ሰላጤ ጋር የነበራት ታሪካዊ ትስስር ከዘመናዊው ፖለቲካዊ አጀንዳ የሚልቅ ነው።

በቀጣናው የባሕር ንግድ ግንኙነቶች እንደነበሯት የጠቀሱት ምሁሩ፣ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር፣ ከሕንድ ውቅያኖስና ከሜዲትራኒያን የንግድ መስመሮች ጋር በመገናኘት የጥንታዊ ንግድ ማዕከል ሆና መቆየቷን ታሪክ ያስታውሳል ብለዋል።

የባሕር በር ባለቤትነቷ በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ከዓለም የንግድ መስመሮች ጋር በማገናኘት፣ በኢኮኖሚያዊ ልውውጥና በዲፕሎማሲያዊ መድረኮች ላይ ንቁና ተጽዕኖ ፈጣሪ ተዋናይ እንድትሆን ትልቅ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

ይሁንና የተፈጸመው ታሪካዊ ስህተት በቀይ ባሕር ዳርቻ የነበረውን የፖለቲካ አቀማመጥ በመቀየር የኢትዮጵያን የባሕር በር አማራጮች እንደገደበ ምሁሩ ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት ግን ኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነቷን ለማረጋገጥ የምታደርገው እንቅስቃሴ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭን ዋነኛ መርህ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ይህንን እውን ለማድረግ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማትን ማሳተፍ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ውጭ ግንኙነት መምህር ኢዶሳ ደገፈ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር አለማግኘቷ በዋናነት በንግድና በኢኮኖሚዋ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

አብዛኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ በባሕር መጓጓዣ የሚከናወን በመሆኑ፣ ሀገሪቱ ለገቢና ወጪ ንግዷ ከፍተኛ የሎጂስቲክስና የማጓጓዣ ወጪ ለማውጣት እንደተገደደች መሆኑን ጠቁመዋል። 

ይህም የሸቀጦችን ዋጋ በማሳደግ በዜጎች ላይ ተጨማሪ የኑሮ ጫና እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

የባሕር በር ተደራሽነትን ማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው የጋራ ደኅንነትም፣ ለኢኮኖሚያዊ ትስስርም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው መምህሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን የፀጥታና የዲፕሎማሲ ሚና በመጠቀም የባሕር በር ተደራሽነት ካረጋገጠች፣ የባሕር ደኅንነትን ለማጠናከር፣ ሽብርተኝነትንና ሕገወጥ ተግባራትን ለመከላከል አዎንታዊ ሚና ሊኖረው እንደሚችልም አስረድተዋል።

የባሕር በር ጥያቄው የጎረቤት ሀገራትን ጥቅምና ፍላጎት ባገናዘበ ሰላማዊ ድርድርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም