በኦሮሚያ ክልል የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል አስደናቂ እመርታ እያስመዘገበ የሚገኘው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የሩዝ ምርት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ሀገሪቱ በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ምርቱን ከውጭ ስታስገባ ቆይታለች።
የውጭ ምንዛሬ ወጪ ለማስቀረትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የኦሮሚያ ክልል ከስንዴ ልማት ባገኘው ስኬታማ ተሞክሮ በመታገዝ፣ ያሉትን ለም መሬቶችና የውኃ ሀብቶች ወደ ልማት በማስገባት የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
ቀደም ሲል በጥቂት ሄክታር መሬት ላይ ብቻ በባህላዊ መንገድ ይመረት የነበረውን የሩዝ ምርት በኩታ ገጠም አስተራረስ እና በዘመናዊ ግብዓቶች በማስፋፋት፣ ክልሉን የሩዝ ምርት ማዕከል ለማድረግ የተያዘው ይህ ኢኒሼቲቭ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው ጀማነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የአርሶ አደሩን ገቢ የሚያሳድጉ ስትራቴጂያዊ ሰብሎች ላይ በተሠራው ሥራ፣ አርሶ አደሮች በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ።
ክልሉ ለሩዝ ልማት ተስማሚ ሥነ-ምህዳር ቢኖረውም ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ፣ እስከ 2013/14 የምርት ዘመን ድረስ ይለማ የነበረው መሬት ከ16 ሺህ ሄክታር እንዳልበለጠና የሚገኘው ምርትም እስከ 805 ሺህ ኩንታል ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ጊዜ ግን የክልሉ መንግሥት በሩዝ ልማት ውጤታማና አመቺ የሆኑ አካባቢዎችን በጥናት በመለየት ኢኒሼቲቩ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በተለይም በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የሩዝ ልማቱ እየተስፋፋ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በክልሉ የሩዝ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የግብዓት አቅርቦት እንዲሳለጥ ከመደረጉም ባለፈ፣ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና እና ሙያዊ ድጋፍና ክትትል መደረጉን አቶ እንዳሻው ገልጸዋል።
በመደመር መንግሥት የተቀረጹ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮች ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ እየቀየሩት መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ከዚህ ውስጥ ደግሞ የሩዝ ልማት ባለፉት ዓመታት ትልቅ እመርታ ማሳየቱን ተናግረዋል።
በክልሉ በ2017/18 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ከለማው የሩዝ ሰብል ወደ 63 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ለአብነት አንስተዋል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከለማው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ደግሞ እስካሁን ከ544 ሺህ 607 ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ የሩዝ ሰብል መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በሩዝ ልማቱ ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ የሩዝ መፈልፈያ/ማቀነባበሪያ ማሽኖች አቅርቦት ላይም በትኩረት መሠራቱን አክለዋል።
አርሶ አደሮቻችንም የደረሰውን የሩዝ ሰብል ወቅቱን ጠብቀው በኮምባይነር እና በባህላዊ የአሳባሰብ ዘዴ ከሰበሰቡ በኋላ በድህረ ምርት የሚፈጠረውን ብክነት በመቀነስ ላይ አጥብቀው መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።