ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች የአፍሪካን የመቻል አቅም በተግባር እያሳየች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች የአፍሪካን የመቻል አቅም በተግባር እያሳየች ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2019(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች የአፍሪካን የመቻል አቅም በተግባር እያሳየች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ሲሆን፤ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከጤናው ዘርፍ ባሻገር የገንዘብ፣ የዕቅድ፣ የግብርና እና የአካባቢ ጥበቃ ዘርፎችን የወከሉ ከ46 በላይ ሚኒስትሮች በጉባኤው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የጉባኤው ታዳሚዎች የኢትዮጵያን ውጤታማ ተግባርና ተሞክሮ እንዲሁም ከጤናው ዘርፍ ባለፈ በሌሎችም መስኮች እያስመዘገበቻቸው ያሉ ሁለንተናዊ ለውጦችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
ይህም ሀገሪቱ ያላትን የመሥራትና የመፈጸም አቅም በተግባር በማሳየት በአህጉሪቱ ላይ እምነት እንዲጣል ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አብራርተዋል።
መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ አጋሮችና የግል ድርጅቶች በጋራ እየተወያዩበት ባለው በዚህ መድረክ፤ ኢትዮጵያ በሳይንስ ዘርፍ ያከናወነቻቸውን ሥራዎች በተለያየ መንገድ እያቀረበች ትገኛለች ብለዋል።
ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ጤና፣ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ እና በሕክምና ሪፈራል ሥርዓት የሠራቻቸውን ውጤታማ ሥራዎች መመልከታቸውን አስረድተዋል።
በተለይም የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የማኅበረሰቡን ጤና በዲጂታል መንገድ የሚከታተሉበትን የኤሌክትሮኒክ የማኅበረሰብ ጤና መረጃ ሥርዓት በተግባር ማየት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በርካታ ሀገራት የኢትዮጵያን ሞዴሎችና የዲጂታል አሠራሮች በሀገራቸው ለመተግበር ፍላጎት ማሳየታቸውንና የልምድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የዓለም የጤና አስተዳደር ሥርዓት እየተቀየረ መሆኑን ያነሱት ዶክተር መቅደስ፤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን ኢትዮጵያ የጤና ዲፕሎማሲን በስፋት እየተጠቀመች መሆኗን ተናግረዋል።
ጉባኤው የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ወደ ተጨባጭ ውሳኔዎች የሚያሸጋግር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የጤና ውይይቶችና በሳይንስ ትግበራዎች ተቀባይ ብቻ ሳትሆን ሰጪም ሆና እየወጣች መሆኗን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በተከታታይ የተካሄዱት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጉባኤዎች ለዚህ መድረክ ስኬት መሠረት መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል።