ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል የቀረበው ነዳጅ ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራጨ ነው

መቀሌ፤ ህዳር 15 /2019 (ኢዜአ)፦  በትግራይ ክልል የቀረበው ነዳጅ ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራጨ መሆኑን በትግራይ ክልል የፌደራል መንግሥት ባላደራ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።


በነዳጅ አቅርቦት ላይ መቆራረጥና እጥረት እንዳይከሰትም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተመላክቷል።

በባላደራ አስተዳደሩ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋይ ግርማይ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለፁት፣  በክልሉ የነዳጅ አቅርቦት መጀመሩን ተከትሎ  በመቐለ ከተማ ከሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።

በዚህም በከተማዋ እስካሁን ድረስ 12ት የነዳጅ ማደያዎች ወደ ሥራ እንደገቡ መደረጉን አንስተው፣ በቀጣይ ወደ ሌሎች የክልሉ ከተሞችም ነዳጅ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የቀረበው ነዳጅ ቅድሚያ ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች እየተሰራጨ መሆኑን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው፣ ዛሬ በመቐለ ከተማ  ነዳጅ ያገኙ ታክሲዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

ይህም በትራንስፖርት ዘርፍ አጋጥሞ የነበረውን ችግር በመፍታት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በቀጣይም በነዳጅ አቅርቦት ላይ መቆራረጥና እጥረት እንዳይከሰት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አቶ ተስፋይ አመልክተዋል።

የትግራይ ክልል የፌደራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር የትራንስፖርትና መገናኛ ቢሮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በመቐለ ከተማ የነዳጅ አቅርቦት በመጀመሩ ምክንያት በከተማዋ አዲስ የታክሲ ትራንስፖርት ታሪፍ መዘጋጀቱን አስታውቋል።

አዲሱን ታሪፍ በታክሲዎች ውስጥ እንዲሁም በትራንስፖርት መጫኛና መውረጃ ቦታዎች ላይ በግልጽ እንደሚለጠፍ ያስታወቀው የቢሮው መግለጫ፣ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችም ከተወሰነው ታሪፍ በላይ ሊከፍሉ እንደማይገባና ይህንን መብታቸውን ጠንቅቀው ማወቅ እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

የተመደበላቸውን ነዳጅ ለትራንስፖርት አገልግሎት በማያውሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ቢሮው አያይዞ ገልጿል።
በቀጣይም የነዳጅ አቅርቦት ወደ ሌሎች የክልሉ ከተሞች ሲዳረስ ከመናኸሪያ ለሚነሳና ወደ መናኸሪያ ለሚገባ የትራንስፖርት አገልግሎት አዲስ የክፍያ ታሪፍ እንደሚዘጋጅ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የትግራይ ክልል የፌደራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር በስድስት ወራት የሥራ ዘመኑ እንዲያከናውናቸው ከተሰጡት ተግባራት መካከል አንዱ የተቋረጡ መደበኛ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለሕዝቡ ተደራሽ ማድረግ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም