ቀጥታ፡

ጉባኤው ሀገራት ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር የሕዝብ ጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያስችል ጉልህ አቅም ይፈጥራል 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15 /2019 (ኢዜአ)፦ 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ሀገራት ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር የሕዝብ ጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያስችል ጉልህ አቅም እንደሚፈጥር የዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ተሳታፊዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የሚቆየውን 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ትናንት በይፋ ከፍተዋል።
 
በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤም “የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ መካሄዱን ቀጥሏል።
 
በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በተዘጋጀው በዚህ ጉባኤ፤ ከ100 በላይ ከሆኑ ሀገራት የተውጣጡ ከ30ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል።

ጉባኤው በሁለተኛ ቀን ውሎው "አህጉራዊ የዝግጁነት፣ የመከላከልና የምላሽ አቅምን ተቋማዊ ማድረግ" በሚል መነሻ ሀሳበ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሯቸውን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ከናይጄሪያ የመጣው ዶክተር ፖሊካርፕ ዳዉዳ ማዳኪ ጉባኤው ከመላው አፍሪካ ከመጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ጋር ልምድ ለመለዋወጥ ያስችሏል ብሏል።

ይህም ሀገራት የየራሳቸውን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል የሚያግዝ ጠቃሚ ዕድል እንደሚፈጥር  ተናግሯል።

በተለይም ሀገራት በሕዝብ ጤና ዘርፍ ስላሉ አዳዲስ ፈጠራዎች፣ የአሠራር ሥርዓቶችና የተለያዩ ተሞክሮዎች በጋራ እንዲወያዩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና ውጤታማ የሆኑ አሠራሮችን ለመለየትና ከየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለመተግበር እንደሚያስችል ጠቁሟል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ከናይጄሪያ የመጣችው ሲሊቪያ ኤዜኔዋ አሀኔን በበኩሏ በአፍሪካ የሕዝብ ጤና ሥርዓት ከሚገጥሙ ዋነኛ ፈተናዎች መካከል የበሽታዎችን በጊዜ የመለየትና የመቆጣጠር አቅም ማጠናከር አንዱ መሆኑን አንስታለች።

እያንዳንዱ ሀገር ጠንካራ የበሽታ ክትትል ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ጠቁማ ይህም የበሽታ ወረርሽኞችን በጅምር ደረጃ ለመለየት፣ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ወረርሽኞች ወደ ሌሎች አካባቢዎችና ሀገራት እንዳይዛመቱ ለመከላከል ወሳኝ ሚና አለው ብላለች።

በጉባኤው ከተለያዩ ሀገራት በተገኙ ባለሙያዎች በሚቀርቡ ጥናታዊ ገለጻዎችና የልምድ ልውውጦች በርካታ ትምህርቶችን እያገኙ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ከማላዊ የተገኙት አቤሴሎም ራኔክስ ናቸው። 

በዘርፉ አዳዲስ አሠራሮች እና ተሞክሮዎች መመልከታቸው የሥራ አቅማቸውንና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል እንደሚያግዛቸው አመልክተዋል።

በጉባኤው የሚገኙ ልምዶችን ወደ የሀገራቸው በመውሰድ ለመተግበርና የሕዝብ ጤና አገልግሎትን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም