ኢትዮጵያ ሁሉም የሱዳን ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ውይይት መድረክ እንዲመጡ ይፋዊ የሠላም ጥሪ ታቀርባለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሁሉም የሱዳን ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ውይይት መድረክ እንዲመጡ ይፋዊ የሠላም ጥሪ ታቀርባለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 15 /2019 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በሱዳን ለአራተኛ ዓመት የዘለቀውን አውዳሚ ጦርነት ለማስቆም እና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ያለመ ይፋዊ የሠላም ጥሪ ለሁሉም የሱዳን ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ሲቪል ኃይሎች አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ሱዳናውያን በራሳቸው ፍላጎት ዘላቂ ሰላም የሚያመጡበትን ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ ለማስተናገድና ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልእክት፣ ኢትዮጵያ ሱዳናውያን ራሳቸው መጻኢ ዕድላቸውን የሚወስኑበትን ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀትና ለመምራት ሙሉ ዝግጁነት እንዳላት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ተሻጋሪ ወንድማማችነት፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ ትስስር እንዲሁም የትውልዶች መስተጋብር ላይ የቆመ ጥልቅ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ሱዳንን እንደ ጎረቤት ብቻ ሳይሆን እንደ ወንድም ሀገርና የተወደደ ሕዝብ እንደምትመለከት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሱዳን እየደረሰ ያለው ጦርነት፣ ውድመትና ሰብዓዊ ሥቃይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕሊና የሚነካ ቁስል መሆኑን አንስተዋል።
እ.ኤ.አ. በ2023 ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ የሱዳንን አንድነት፣ ሰላምና ደኅንነት በሚያስከብር መልኩ ግጭቱን ለማስቆም ተከታታይ ጥረቶችን ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።
ይህ ጥረትም እ.ኤ.አ. በ2019 በነበረው የሽግግር ወቅት በሲቪልና በወታደራዊ አካላት መካከል ስምምነት እንዲደረስ ኢትዮጵያ ከተጫወተችው ቀዳሚ ሚና የቀጠለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ወሳኝ ታሪካዊ ወቅት ጦርነቱን ለማስቆምና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያስተናግደውና በሚደግፈው ሁሉን አቀፍና ግልጽ የሠላም መድረክ ላይ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ሲቪል አካላትን ጨምሮ ሁሉም የሱዳን ወገኖች እንዲሳተፉ ይፋዊ ጥሪ መቅረቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ይህ የሰላም ተነሳሽነት ብቸኛው ዓላማ ለሱዳንን ሕዝብ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እንዲሁም ሱዳንን ከጥፋት መታደግ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ፍጹም ገለልተኝነቷን ጠብቃ፣ ሱዳናውያን ያለምንም ውጫዊ ጫና ልዩነቶቻቸውን በመግባባት የሚፈቱበት ግልጽና መከባበር የሰፈነበት የውይይት መድረክ ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ይህም የሱዳናውያን ክብር የሚጠብቅ፣ የሀገሪቱን አንድነትና ብዝኃነት የሚያስከብር አዲስ ብሔራዊ ቃል ኪዳን ለመቅረጽ ብቸኛው መንገድ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ግቡ የአንዱ ወገን በሌላው ላይ ድል መቀዳጀት ሳይሆን ደም ማፋሰስን ማስቆምና ሱዳናዊያንን አሸናፊ ማድረግ መሆኑን ነው ያብራሩት።
የሱዳን መጻኢ ዕድል በሱዳናውያን ብቻ የሚወሰን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህ ረገድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ወዳጅ ሀገራትና ቀጣናዊ ድርጅቶች የተጎጂዎችንና የተፈናቃዮችን ሥቃይ ለማቃለል የሚደረጉ ሰብዓዊ ጥረቶችን እንዲያጠናክሩ ኢትዮጵያ ትጠይቃለች ብለዋል።
ኢትዮጵያም ለዚህ የሰላም ተነሳሽነት ስኬት የዲፕሎማሲ አቅሟንና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶቿን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ የሱዳንን ሰላም እንደ ራሷ ደኅንነትና መረጋጋት እንደምትመለከተው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሱዳን መረጋጋትም ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ሰላም የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ የሰላም ጥሪ እውነተኛ ጉርብትና በፈተና ወቅት እንደሚመዘን የሚያመላክት፣ እንዲሁም የሁለቱን ሕዝቦች የጋራ ትስስር ከጊዜያዊ ልዩነቶች በላይ እንደሚልቅ የሚያጸና ቅን የወንድማማችነትና የሰብዓዊነት ጥሪ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሁሉም የሱዳን ወገኖች የሀገራቸውን በማስቀደምና ሀገራዊ ኃላፊነትን በመላበስ ለዚህ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ኢትዮጵያ ሙሉ ተስፋ እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሱዳናዊያን ሰላምና ደህንነት እንደሚገባቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያም ይህ እንዲሳካ ከሱዳናዊያን ጎን እንደምትቆም አረጋግጠዋል።