ቀጥታ፡

የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ሴኔጋል በአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮንነቷን እንድትቀጥል ወሰነ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15 /2019 (ኢዜአ)፦ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (CAS) ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ሆና እንድትቀጥል ውሳኔ አስተላለፈ።

ውሳኔው የተሰጠው በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ሴኔጋል ሞሮኮን በተቃውሞ ሜዳ ለቅቃ ከወጣች በኋላ በተጨማሪ ሰዓት አሸንፋ የነበረውን ድል የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ገልብጦ ለሞሮኮ የ3 ለ 0 ድል ከሰጠ በኋላ በተነሳው ውዝግብ ላይ ነው።

የፍጻሜው ጨዋታ በመደበኛው ክፍለ ጊዜ የመጨረሻ ደቂቃ ለሞሮኮ ፍጹም ቅጣት ምት በመሰጠቱ የተነሳ ሴኔጋሎች ሜዳ ለቅቀው በመውጣታቸው ለ15 ደቂቃ ያህል ተቋርጦ ነበር።

በስታዲየሙ ውጥረት እየጨመረ በነበረበት ወቅት የሴኔጋል ኮከብ አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ቡድኑ ወደ ሜዳ እንዲመለስ ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፤ ዳኛው ዣን-ዣክ ንዳላ ጨዋታውን ሲያስጀምሩ የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ የመታውን ፍጹም ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው አድኖበታል። በመጨረሻም ሴኔጋል በተጨማሪ ሰዓት ፓፔ ጉዬ ባስቆጠራት ግብ 1-0 አሸንፋለች።
የእግር ኳስ ህጎች የዳኛ ውሳኔ የመጨረሻ መሆኑን ቢደነግጉም፣ የካፍ ይግባኝ ሰሚ ዳኞች የአፍሪካ ዋንጫ ደንብን በመጥቀስ አንድ ቡድን ያለ ዳኛው ፈቃድ ጨዋታ ሳያልቅ ሜዳ ለቅቆ ከወጣ እንደተሸነፈ እንደሚቆጠርና ከውድድሩ እንደሚሰረዝ በመግለጽ ውሳኔ ሰጥተው ነበር።

ካፍ በተጨማሪም በሁለቱ እግር ኳስ ማህበራት፣ በተጫዋቾች እና በወቅቱ የሴኔጋል አሰልጣኝ በነበሩት ፓፔ ቲያው ላይ ከ1 ሚሊዮን ዶላር (770,000 ፓውንድ) በላይ የገንዘብ ቅጣት ጥሎ ነበር።
የሴኔጋል እግር ኳስ ማህበር የካፍን ውሳኔ በመቃወም ጉዳዩን ወደ ስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (CAS) በመውሰድ ድሉ እንዲመለስላት ይግባኝ ብሎ ነበር።

በዚህ መሠረት የፍርድ ቤቱ ዳኞች በአንድ ቀን ችሎት ማስረጃዎችንና ክርክሮችን አዳምጠው የመጨረሻውን ብይን ሰጥተዋል።

የዛሬው ውሳኔ የአፍሪካ እግር ኳስን ለወራት ሲያወዛግብ የነበረውን የሻምፒዮንነት ጥያቄ እልባት ሰጥቷል።

በዚህም ሴኔጋል በሜዳ ላይ ያገኘችውን የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮንነት በይፋ መልሳ አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም