ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት የእናቶችና ሕጻናትን የጤና ሥርዓት በማሻሻል በኩል አስደናቂ ውጤት እያስገኘ ነው - የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15 /2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የእናቶችና ሕጻናትን የጤና ሥርዓት በማሻሻል አስደናቂ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በምግብና ሥነ-ምግብ ሥርዓት ላይ አመርቂ የምርታማነት ውጤት እያስገኘ ነው።

ይህ መርሐ-ግብር የወተት፣ የእንቁላል፣ የዶሮ፣ የማርና የዓሣ ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደጉ እናቶችና ሕፃናት የተመጣጠነ ከእንስሳት ተዋጽኦ የሚገኝ ንጥረ-ምግብ እንዲያገኙ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።

በተጨማሪም ቤተሰቦች የቤት ወጪያቸውን በመቀነስና ገቢያቸውን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሕፃናትን ከተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ከመቀንጨር እየታደገ ይገኛል።

በሌላ በኩል የሰቆጣ ቃል ኪዳን የጤና፣ የግብርና፣ የውኃና የትምህርት ዘርፎችን በቅንጅት በማስተባበር በእርግዝና ወቅትና ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት የሥርዓተ ምግብና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን አጠናክሯል።

በዚህም የማኅበረሰቡን የአመጋገብና የንጽሕና አጠባበቅ በማሻሻል የሕፃናትን መቀንጨር ለመቀነስና ጤናማ ትውልድ ለመገንባት ተጨባጭ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የሚቆየውን 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ትናንት በይፋ ከፍተዋል።

በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የተከፈተው ጉባኤም “የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ መካሄዱን ቀጥሏል።

የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን በጉባኤው መክፈቻ ወቅት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ኢትዮጵያ የተገበረቻቸው ተነሳሽነቶች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።

ለአብነትም የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርና የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ተነሳሽነቶች በውጤታማነት በማስቀጠል የእናቶችና የሕፃናትን ጤና በመጠበቅ በኩል አመርቂ ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የሥርዓተ-ምግብ ሁኔታንና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሂደት ጉልህ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ራእይና የአመራር ሰጪነት የልማት ተነሳሽነቶቹ ላስመዘገቡት እመርታዊ ውጤት አድንቀዋል።

የጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ሴራሊዮን፣ ቡሩንዲ፣ የናሚቢያና የሌሶቶ መሪዎችም በአህጉሪቱ የጤና፣ የሥርዓተ-ምግብና የሰው ተኮር ልማት ለማሻሻል ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

የአህጉሪቱን የጤና፣ ምግብና ሥነ-ምግብ ሥርዓት ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶች የእናቶችና ሕፃናትን ጤና በመጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በቀጣይም የአፍሪካን የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነት በማጎልበት ጤናማና አምራች ዜጋን ማፍራት የሚያስችል መሰል ተነሳሽነቶች እና ኢንቨስትመንት ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም