ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ለአፍሪካ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትና ለጋራ ዕድገት ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ያጠናክራሉ- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ለአፍሪካ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትና ለጋራ ዕድገት ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ያጠናክራሉ- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 15 /2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ለአፍሪካ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትና ለጋራ ዕድገት ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር እንደሚያጠናክሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከ5ኛው የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ጉባዔ ጎን ለጎን ከዩጋንዳ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄሲካ አሉፖ ጋር የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለአፍሪካ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የልማት ፈተናዎችን ለመፍታት ወሳኝ አቅም እንዳለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
ይህንን አቅም ለማሳደግ በራሳችን ቋንቋዎች፣ እውቀትና እውነታዎች ላይ የተመሠረቱ ቴክኖሎጂዎችን ማበልጸግ፣ የምርምርና የፈጠራ አቅማችንን ማጠናከር ይጠይቃል ሲሉ ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍም ሰው ሰራሽ አስተውሎት የባለሙያዎችን አቅም በመደገፍና የአገልግሎት ተደራሽነትን በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
ለዚህም ከአፍሪካዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣሙ መፍትሔዎችን ማዘጋጀትና የመረጃ ደህንነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እና በአዳዲስ የምርምርና የትምህርት ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ በመመሥረት፣ ከዩጋንዳና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በቴክኖሎጂ፣ በጋራ ምርምርና በእውቀት ልውውጥ ያለንን ትብብር ማጠናከር ለጋራ ዕድገታችን ወሳኝ ነው ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።