ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ያስመዘገበችው ዕድገት ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮና አርአያ ነው - የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሲካ አሉፖ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ያስመዘገበችው ዕድገት ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮና አርአያ ነው - የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሲካ አሉፖ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ያስመዘገበችው ዕድገትና የፈጠራ አቅም ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮና አርአያ መሆኑን የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሲካ አሉፖ ገለጹ፡፡
በ5ኛው የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ጉባኤ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የሚገኙት የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሲካ አሉፖ ከኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።
የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሲካ አሉፖ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ያስመዘገበችው ዕድገትና የፈጠራ አቅም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮና አርአያ የሚሆን ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ትምህርትን ከመስጠት ባለፈ ቴክኖሎጂውን በተጨባጭ ሕይወት ውስጥ በፍጥነት በመተግበሩ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጂውን ገና ያላላመዱ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ኢንስቲትዩቱ በመምጣት ልምድ መቅሰም አለባቸው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኡጋንዳ በአሁኑ ወቅት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ በመቅረጽ ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ይህ ጉብኝት ቴክኖሎጂውን በግብርና፣ በጤና፣ በሳይንስና በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያፋጥነው ገልጸዋል።
በኢንስቲትዩቱ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አፍሪካውያን ሳይንቲስቶች ለራሳቸውና ለአህጉሪቱ ዕድገት ትልቅ አቅም እንዳላቸው የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።