አየር ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባሻገር ዘመናዊ ተቋማዊ አቅሙን በመገንባት ዘርፈ ብዙ ድሎችን እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባሻገር ዘመናዊ ተቋማዊ አቅሙን በመገንባት ዘርፈ ብዙ ድሎችን እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2019(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገርን ሉዓላዊነትና ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት ከመወጣት ባሻገር በልማት ስራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል 91ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ሁለተኛው የቢሾፍቱ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ህዳር 20 ቀን 2019 እንደሚካሄደም ተጠቁሟል፡፡
የኢፌዴሪ አየር ኃይል 91ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደውን የ10 ኪሎ ሜትር ዓለም ዓቀፍ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመገናኛ ብዙሃን ተሰጥቷል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፣ አየር ኃይል እንደ አንድ የመከላከያ አካል ሀገርን በመከላከል፣ በመጠበቅ እና ጠላትን በማጥፋት ድል እያስመዘገበ ቀጣይ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ ግዳጅ እየተወጣ ሀገርን በማልማት፣ ተቋም በመገንባት እና የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ባለፈው ዓመት የተቋሙ የምስረታ ቀን አስመልክቶ ለቢሾፍቱ ከተማ እንደ አንድ ብራንድ ተጀምሮ የነበረው የአየር ኃይል ታላቁ የጎዳና ላይ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ በዘንድሮው በዓልም እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በሩጫው ላይ ሰራዊቱ እና የአካባቢው ማህበረሰብ እንደሚሳተፉ ጠቁመው፤ ይህንን መግለጫ የሚከታተሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ተወጣጥተው በመምጣት አብረው እንዲሮጡ እና በዓሉን በደመቀ ሁኔታ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ሽመልስ ዳዊት በበኩላቸው በውድድሩ ላይ ከ10 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ጠቁመው ከ800 በላይ የሚሆኑ ኢሊት አትሌቶች እንዲሁም በኦሎምፒክ፣ በዓለም ሻምፒዮና እና በጎዳና ሩጫዎች ተሳትፈው ትልቅ ድል ያስመዘገቡ ታላላቅ አትሌቶች እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የውድድሩን ሽልማት በተመለከተ ሲያብራሩ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ለሚወጡ አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች (በወንድም በሴትም) ተመሳሳይ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት 1ኛ ለሚወጣ አትሌት 500 ሺህ ብር (በወንድም በሴትም) 2ኛ ለወጣ አትሌት 250 ሺህ ብር (በወንድም በሴትም) 3ኛ ለሚወጣ አትሌት 150 ሺህ ብር (በወንድም በሴትም) መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም 1ኛ በመውጣት አሸናፊ የሆኑ አትሌቶችን ለአሰልጠኑ አሰልጣኞች እያንዳንዳቸው የ100 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።