በአማራ ክልል በ9 ሺህ 568 ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል-ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በ9 ሺህ 568 ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል-ቢሮው
ባህር ዳር ህዳር 15/2019 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በዘንድሮው በጋ በ9 ሺህ 568 ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለማከናወን ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
በመደመር መንግስት አሳቤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ በተከናወኑ ሰፊ የተፋሰስ ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች አማካኝነት በአካባቢ ጥበቃ፣ በግብርና እና በኢኮኖሚ ዘርፎች በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ከነዚህ መካከል የአፈር መሸርሸርን መከላከል እና የመሬት ለምነት መመለስ፣ የደን ሽፋን መጨመር እና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መጥቷል።
በተጨማሪም ለውሃ ሀብት መጎልበት፣ ለግብርና ምርታማነት ማደግና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እንዲሁም ለስራ ዕድል ፈጠራ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።
በተፋሰስ ልማት መልሰው ባገገሙ አካባቢዎች ዜጎች በችግኝ ማፍላት፣ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት ማድለብ እና በፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ እየሆኑም ናቸው።
የተፋሰስ ልማት ሰራው በየአመቱ በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እና በበጎ ፈቃድ መንፈስ የሚከናወን በመሆኑ በማህበረሰቡ ዘንድ የጋራ ንብረትን የመጠበቅ ባህልንና ማህበራዊ ትስሰርን እንዲጎለብት አድርጓል።
እንደ አማራ ክልልም ባለፉት ዓመታት በ8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተከናውኗል።
በዚህም የአፈር ለምነትን ከማሻሻል ባለፈ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በደን ማልበስ የተቻለ ሲሆን ልማቱም የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምር በማድረግ ለመስኖ ልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። የአፈር አሲዳማነት እንዲቀንስና የሰብል ምርታማነት እንዲሻሻል አድርጓል። በለሙ ተፋሰሶችም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል።
በዚህ ረገድ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በለሙ ተፋሰሶች አርሶ አደሩ ማንጎ፣ አቦካዶ፣ ፓፓያና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በማልማት ከሚያገኘው የምርት ሽያጭ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆኑም ተመላክቷል።
በክልሉ በዘርፉ የተገኘውን ውጤትና ተሞክሮ በማስፋት በዘንድሮ የበጋ ወራት በህዝብ ተሳትፎ የልማት ስራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራው በ9 ሺህ 568 ተፋሰሶች እንደሚካሄድ ጠቁመው የልማት ስራው በታህሳስ ወር 2019 ዓ.ም እንደሚጀመር አመላክተዋል።
በተፋሰስ ልማት ስራው በ530 ሺህ 397 ሄክታር መሬት ላይ የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን፣ የቦረቦር ማዳን፣ የክትርና የውሃ ማስረጊያ ስትራክቸሮች እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል።
ለስራው የሚያስፈልጉ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አካፋ፣ ዶማና ሌሎች የስራ መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ከ151 ሺህ ለሚበልጡ ቀያሽ አርሶ አደሮች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
ዘንድሮ በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በአደረጃጀት እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የእስቴ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዓለሙ መንግስቴ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በቀበሌው የተከናወነ የተፋሰስ ልማት ለእንስሳት ዋነኛ የመኖ መገኛ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም የመሬትን መሸርሸር በማስቀረት በሄክታር ከገብስ ሰብል እስከ ሶስት ኩንታል ተጨማሪ ምርት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ያስገኘላቸውን ጠቀሜታ ለማስቀጠል ዘንድሮ ለሚካሄደው የልማት ስራ መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የወርዳው ነዋሪ አርሶ አደር መላኩ ስሜነህ ናቸው።