በአሪ ዞን 12 ሺህ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት ሥራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአሪ ዞን 12 ሺህ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት ሥራ ተጀመረ
ጂንካ፤ ሕዳር 15/219 (ኢዜአ)-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን 12 ሺህ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት ሥራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደተግባር መገባቱም ተመላክቷል።
የመደመር መንግስት ለኢኮኖሚው ዋነኛ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል።
ዘርፉን ከባህላዊ የዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ወደ ዘመናዊ፣ በመስኖ እና በቴክኖሎጂ ወደታገዘ አሰራር ለማሸጋገር የፖሊሲና የተግባር ሥራዎችንም አበክሮ ሲሰራ ቆይቷል።
ከውጭ የሚገባን ማዳበሪያ ለመቀነስና በሂደትም ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ ከመስራት ባለፈ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘመናዊ ግብርናን በማስፋፋት የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖውን ተቋቁሞ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚተገበሩ ስልቶች አንዱ የእርሻ ሥራውን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅና የግብርና ግብአቶችን መጠቀም ነው።
ለዚህም አርሶ አደሮች የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውሃ አማራጮችን ተጠቅመው ዓመቱን ሙሉ ማምረት እንዲችሉና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖውን እንዲቋቋሙ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮችም ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው በመስኖ ልማት በመሳተፍ ምርታማነትና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ ለኢዜአ እንደገለጹት የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ ማምረት እንዲቸል አቅም ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
በዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማትም 12 ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
በልማቱም የበጋ መስኖ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ጤፍና መሰል ሰብሎችና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
የበጋ መስኖ ልማት ሥራውን ውጤታማ ለማድረግም በዩኒየኖች አማካኝነት ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨቱን ገልጸዋል።
ከዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት ከ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም ኃላፊው አቶ ጉራልቅ አስታውቀዋል።
በአሪ ዞን የባካ ዳውላ አሪ ወረዳ አርሶ አደር ማርቆስ አዲሱ እና ታሪኩ ማላ በበኩላቸው እንደገለጹት በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ፣ ማሽላና በቆሎ በስፋት ለማልማት አቅደው እየተዘጋጁ ነው።
በአሁኑ ወቅትም በመኸር አዝመራ የለሙና የደረሱ ሰብሎችን በማንሳት የማሳ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የእርሻ ሥራቸውን የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቀው ሲያከናውኑ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህም ከወቅቶች መዘበራረቅ አኳያ በሚፈለገው መጠን ውጤታማ እንዳላደረጋቸው ተናግረዋል።
በመስኖ ልማት ላይ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ የከርሰ ምድርና ወራጅ ወንዞችን ወደማሳቸው በመጥለፍ፣ እርጥበትን በማቆየትና ውሃን በማከማቸት የእርሻ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ባከናወኗቸው የመስኖ ልማት ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።