ቀጥታ፡

የእናት ጡት ወተት ባንክ -- ለጨቅላ ሕጻናት አዲስ የሕይወት ተስፋ

(በሀብታሙ መኮንን - ሀዋሳ ኢዜአ ቅርንጫፍ)

ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱ ጨቅላ ሕጻናት ለተለያዩ ውስብስብ የጤና እክሎች እንደሚዳረጉ የጤና መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይ በጤና ችግርም ሆነ በተለያየ ምክንያት ቀናቸው ሳይደረስ የሚወለዱ ሕጻናት የወላጆቻቸው ጡት ወተት በማያመነጭበት ጊዜ ሕጻናቱ ለተለያየ ችግር ይጋለጣሉ። እነዚህን ጨቅላ ሕጻናት ከተለያዩ ውስብስበ የጤና ችግሮች ለመታደግና ሕይወታቸውን ለማትረፍ ደግሞ የጡት ወተት አስፈላጊ ነው።

እስከዛሬ ይህን ችግር ለመፍታት ወላድ እናቶች ጡት ማጥባት በማይችሉ ጊዜ በጎረቤት ያለች ጡት የምታጠባ ሌላ እናት ተፈልጋ ጨቅላ ሕጻኑን እንድታጠባ ይደረጋል። በህብረተሰቡ ውስጥ ይህ ባህላዊ ልምድ ቢኖርም በአካባቢው የምታጠባ እናት በማትኖርበት ጊዜ ግን ሕጻኑ ለጉዳት መዳረጉ አይቀርም። ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው የሕጻናት ሀኪሞች የጡት ወተት ባንክን ማቋቋም ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን በመረዳት ባንኩን እንዲቋቋም አደርገዋል።

ከረጅም የዘልማዳዊ ሥርዓት በኋላ በኦስትሪያ ቪየና ዩኒቨርሲቲ የሕፃናት ሕክምና ባለሙያ የነበሩት ዶክተር ቴዎዶር ኤሸሪች የእናት ጡት ወተት ለጨቅላ ሕፃናት አንጀት ጤና እና ሕይወት መትረፍ ወሳኝ ሚና እንዳለው በጥናት አረጋግጠዋል። ይህን ተከትሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ100 ዓመታ በፊት የመጀመሪያው የእናት ጡት ወተት ባንክ በኦስትሪያ ቪየና እንዲቋቋም ተደርጓል።

እ.አ.አ በ1909 በዶክተር ቴዎዶር ኤሸሪች ጥረት የዓለም የመጀመሪያው የጡት ወተት ባንክ እውን ቢሆንም ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ በአሜሪካ ቦስተን እ.አ.አ በ1910 በአሜሪካ የመጀመሪያው፤ በዓለም ደግሞ ሁለተኛው ባንክ ተከፈተ፡፡ በሂደትም ሌሎች የዓለም ሀገራት ይህንን ዘመናዊ የጡት ወተት ባንክ በመክፈት ለአገልግሎት ማብቃታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ሆኖም በ1960ዎቹ የዱቄት ወተት (Formula) መስፋፋትን ተከትሎ የባንኮቹ ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል። ይሁን እንጂ የዓለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ በ1980 እ.ኤ.አ. የሕጻኑ ወላጅ እናት ማጥባት ካልቻለች ከለጋሾች የሚገኝ የጡት ወተት ተመራጭ መሆኑን በይፋ አወጁ። 

በቀጣዮቹ ዓመታ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ (HIV/AIDS) ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ የእናት ጡት ባንኮች ቢዘጉም የለጋሾች የደም ምርመራ እና ወተቱን በሙቀት የማከም (Pasteurization) ጥብቅ ደረጃዎች ላይ በመደረሱ ዘርፉ በአዲስ መልክ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተደርጓል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ከ66 በሚበልጡ የዓለም ሀገራት ውስጥ ከ750 በላይ የእናት ጡት ወተት ባንኮች በሥራ ላይ ይገኛሉ። አገልግሎታቸውም ያለ ዕድሜያቸው ለተወለዱ፣ ክብደታቸው ዝቅተኛ ለሆነ እና በተለያዩ ምክንያቶች የእናታቸውን ጡት ወተት ማግኘት ለማይችሉ ጨቅላ ሕፃናት ሕይወትን ማዳን ነው።

ወደ አህጉራችን አፍሪካ ስንመጣ ደግሞ በአፍሪካ የጡት ወተት ባንክን በማቋቋም ፈር ቀዳጇ ደቡብ አፍሪካ ነች፡፡ የመጀመሪያው የጡት ወተት ባንክ የተከፈተው በሀገሪቱ ደርባን ከተማ ሲሆን ይህ የሕፃናት አድን ተግባር በሌሎች ከተሞችም የተስፋፋ ሲሆን በአሁን ወቅት በሀገሪቱ የባንኮቹ ቁጥር ከ20 በላይ ደርሷል።

በአፍሪካ ምንም እንኳን የጨቅላ ሕፃናት ሞት ከፍተኛ ቢሆንም አገልግሎቱ የተጀመረው በጣም ዘግይቶ መሆኑ ይነገራል። በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የጡት ወተት ባንክ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ አንጎላ፣ ካሜሩን፣ ሞዛምቢክ፣ ኡጋንዳ እና ኬፕ ቨርዴ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የመደመር መንግስት ለጤናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን የማሻሻል፣ የጨቅላ ሕፃናትና የእናቶችን ሞት የመቀነስና ሌሎች ቁልፍ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ2018 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን በአፍሪካ ደግሞ ዘጠነኛውን የወተት ባንክ ከፍቶ ሥራ አስጀምሯል፡፡ በሆስፒታሉም የጡት ወተት ባንክ አገልግሎት ያገኙ እናቶች ትልቅ  እፎይታ ማግኘታቸውን ነው የሚገልጹት።

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል ቤተልሔም ቡርጉዴ አንዷ ናት። "ልጄን ስወልድ ገና ሰባት ወርም አልሞላትም" የምትለው ቤተልሔም፣ ህጻኗ በሕይወት ትቆያለች የሚል ተስፋዋም የተሟጠጠ እንደነበር ታስታውሳለች።

የወለደቻትን ጨቅላ ሕጻን ጡት ማጥባት ባለመቻሏ እርሷና ባለቤቷ ከፍተኛ ድንጋጤና ጭንቀት ውስጥ ገብተው የነበረ ቢሆንም ሕጻኗ ከባንኩ ባገኘችው የጡት ወተት ጤናዋ ተስተካክሎ በማየታቸው መደሰታቸውን ትናገራለች።

ቤተልሔም እንባና ሳቅ በተቀላቀለበት ስሜት ውስጥ ሆና የወተት ባንኩንና በሆስፒታሉ የረዷትን ሀኪሞች ልጇን በሕይወት ስላቆዩላት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች፡፡

ለተወሰኑ ጊዜያት በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ክፍል ውስጥ የቆየው ልጇ አሁን ጤናማ መሆኑን የተናገረችው ቤተልሔም፣ እሷም በአሁኑ ወቅት በተራዋ የሌሎችን ሕፃናት ሕይወት የመታደግ ተግባር እያከናወነች ትገኛለች፡፡

ከልጇ የሚተርፈውን ወተት ለሌሎች ሕጻናት በመለገስ ያኔ ጭንቅ ውስጥ በነበረችበት ወቅት በልቧ ቃል የገባችውን ዛሬ በተግባር እያሳየች ነው፡፡

ሌላኛዋ እናት ወይዘሮ መቅደስ ብሩ ደግሞ በደም ግፊትና ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ሳቢያ ልጃቸውን ያለ ቀኗ ለመውለድ ተገደው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ ከነበራቸው ሕመም በተጨማሪ ጡታቸው ወተት መስጠት ባለመጀመሩ ልጃቸው ከባንኩ ደህንነቱ የተጠበቀ ወተት ማግኘት መቻሏ ትልቅ እፎይታን እንደሰጣቸው ነው የሚገልጹት። ከልጃቸው የሚተርፈውን የጡት ወተት እርሳቸውም በተራቸው በመለገስ  የሌሎች ሕጻናት ሕይወት እየታደጉ ይገኛሉ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ፍፁም ወልደገብርኤል በበኩላቸው የሀዋሳ የእናት ጡት ወተት ባነክ የጨቅላ ሕፃናትን ሞትና ውስብስብ የጤና እክሎች በማስቀረት ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ነው የገለጹት። ባንኩ በተለይ ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ሕፃናት የእናታቸውን ጡት ወተት የማግኘት ዕድል ስለማይኖራቸው የደም መመረዝ፣ የአንጀት ቁስለትና ሌሎች የጤና እክሎች እንዳይገጥማቸው ይታደጋቸዋል ብለዋል።

ባንኩ ሲመሰረትም የነዚህን ሕፃናት ሕይወት የመታደግ ዓላማ ይዞ ነው የተመሰረተው። እንደ ዶክተር ፍጹም ገለጻ በአሁን ወቅት በኮሌጁ ሆስፒታሉ ተኝተው ለሚገኙ እንዲሁም ከሌሎች ሆስፒታሎች በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት ለሚመጡ ጨቅላ ሕፃናት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ባንኩ የጡት ወተቱን የሚያገኘው ፈቃደኛ ከሆኑ እናቶች ከልጃቸው የሚተርፈውን የጡት ወተት በልገሳ በማሰባሰብ ሲሆን ለዚህም አስፈላጊውን ምርመራ ይደረጋል። ከበጎ ፈቃደኞች የተለገሰው ወተቱ ባክቴሪያና ቫይረስን የማስወገጃ ቴክኖሎጂ ሥርአት ውስጥ አልፎ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዲቀመጥ ይደረጋል።

አስፈላጊውን ሂደት አልፎ ደህንነቱ የተረጋገጠ የእናት ጡት ወተት በነጌቲቭ 20 ዲግሪ ሴልሼስ በማቀዝቀዣ ማሽን ውስጥ ለስድስት ወራት ያክል ተቀምጦ ሊቆይ ይችላል። አስፈላጊ በሆነ ጊዜም የእናታቸውን ጡት ወተት ማግኘት ላልቻሉ ሕጻናት በጥንቃቄ እንዲሰጥ ይደረጋል።

የጡት ወተት ባንክ የጭቅላ ሕፃናትን ሕይወት ከመታደግ አኳያ የሚጫወተው ሚና የላቀ በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት በመሰጠት ወደ ሌሎች የጤና ተቋማት እና አካባቢዎች የማስፋት ሥራ ሊሰራ ይገባል መልዕክታችን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም