በባምባሲ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ጽዱ እንዲትሆን አድርጓታል - ኢዜአ አማርኛ
በባምባሲ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ጽዱ እንዲትሆን አድርጓታል
ባምባሲ፤ ህዳር 15/2019(ኢዜአ)፦ በባምባሲ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ጽዱ እንዲትሆን አድርጓታል ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ከሚገኝባቸው ከተሞች አንዷ በሆነችው ባምባሲ ከተማ የ2 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገድ፣ አረንጓዴ ቦታዎችና የህጻናት መዝናኛን ያካተተ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የመንገድ ላይ ኤሌክትሪክ ዝርጋታ እየተከናወነ ነው።
የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተናገሩት የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ለኑሮ እና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የበለጠ ምቹ እንዲትሆን አድርጓታል።
የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት መምህር ጀምበር ጣሰው እንዳሉት የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ ከዚህ በፊት የነበረውን የመንገድ እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ችግር የቀረፈ እና አዲስ ገፅታ የፈጠረ ነው።
በተለይም በከተማዋ ያለው ዋና መንገድ ለተሽከርካሪዎች እና ለእግረኞች ምቹ ባለመሆኑ በየጊዜው የትራፊክ አደጋ እንደሚከሰት አስታውሰው፤ አሁን ግን የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገድን በመለየት የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ እያደገ መምጣቱን የገለፁት መምህር ጀምበር፤ በዚህም የስራ ፈጠራ እና ገቢ ማስገኛ ስራዎች እየተስፋፉ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አርደሻም አህመድ በበኩላቸው፥ በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎቿ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ህብረተሰቡ በልማቱ በንቃት እየተሳተፈ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላትን ተመራጭነት የበለጠ የሚያጎላ እና የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ ለህፃናት እና ወጣቶች ማራኪ የመዝናኛ ቦታዎች እንዲገነቡ በማድረግ ከዚህ በፊት የነበረውን የከተማዋን ገፅታ የቀየረ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አብዱልከሪም አብዱላሂ ናቸው።
የባምባሲ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ ሀሚስ ቢሻራ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱን በጥራት እና ፍጥነት በማከናወን ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በከተማዋ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የመጀመሪው ዙር የኮሪደር ልማት በአመራሩ እና ህብረተሰቡ ተሳትፎ የተከናወነ መሆኑን ገልጸው፥ ህብረተሰቡ የልማቱ ተባባሪ በመሆኑ ስራው በአሁኑ ሰዓት እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል።