ቀጥታ፡

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ40 በላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት በፀሐይ ሃይል አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

ሰቆጣ ህዳር 15/2019(ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከ40 በላይ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተቋማት በፀሐይ ሃይል አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ውኃና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የመጠጥ ውሃ ግንባታ ክትትል ባለሙያ አቶ ታደሰ አዳነ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በብሄረሰብ አስተዳደሩ የውሃ፣ ጤናና ትምህርት ተቋማትን በታዳሽ ሃይል ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው።

ቀደም ሲል የውሃ ተቋማቱ በነዳጅ አማካኝነት ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በዚህም ለጥገናና ሌሎች ወጪዎችን የሚጠይቁ በመሆናቸው ለህብረተሰቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ምክንያት ሆነው ቆይተዋል።

ተቋማቱ በፀሐይ ሃይል አማካኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግም የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱ ያለምንም መቆራረጥ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በቀጣይም በርካታ የውሃ ተቋማትን በፀሐይ ሃይል እንዲሰሩ የማስቻል ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠል ከአጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ የታዳሽ ሃይል የማስፋት ስራ ከውሃ ተቋማት ባሻገር በገጠር የሚገኙ የጤናና ግብርና ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተተገበረ እንደሚገኝም አክለዋል።

በዝቋላ ወረዳ የሚሽራ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ወልዴ እንዳሉት፤ በአካባቢያቸው የሚገኘው የውሃ ተቋም የመሳቢያ ሞተር በተደጋጋሚ ለብልሽት እንደሚጋለጥ አስታውሰው፤ በዚህም የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መቆራረጥ ነበረ ብለዋል።

አሁን ላይ በፀሐይ ሃይል አማካኝነት መስራት ከጀመረ ወዲህ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ወጥ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

ወይዘሮ ኮለ ዘነበ በበኩላቸው፤ በአካባቢያቸው ዘላቂ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ምክንያት ደህንነቱ ያልተጠበቀ ውሃ ለመጠጥነት ይጠቀሙ እንደነበር አውስተዋል።

የፀሐይ ሃይልን መሰረት በማድረግ የውሃ መሰረተ ልማት በአካባቢያቸው ተደራሽ ከሆነ ወዲህ ድካምና እንግልት እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ከሁለት ሺህ በላይ የውሃ ተቋማት እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም