ቀጥታ፡

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ተከናውኗል

ሰቆጣ፤ ሕዳር 15/2019(ኢዜአ)፦ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከ84 ሺህ በላይ ሰዎችን ከወባ በሽታ ለመከላከል የሚያስችል የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት መከናወኑን የብሔረሰቡ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የወባና ትንኝ ወለድ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ አበበ በለጠ እንዳሉት፣ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ጋር ተያይዞ የወባ በሽታ ስርጭት ተስተውሏል።

የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልም ህብረተሰቡን በማሳተፍ የአካባቢ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ ከመስራት ባለፈ ኬሚካል በመርጨት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የወባ በሽታ ሥርጭት በስፋት በሚስተዋልባቸው አርገሌ እና ሰሃላ ወረዳዎች በ30 ሺህ 327 መኖሪያ ቤቶች ላይ የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት መከናወኑን ገልፀዋል።

የበለጠ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በተካሄደ የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት ከ84 ሺህ በላይ ዜጎችን ከወባ በሽታ ለመከላከል እንደተቻለም አስታውቀዋል።

ወቅቱን ባልጠበቁ ዝናብ ምክንያት ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በየሳምንቱ አርብ ቀን ህብረተሰቡን በማሳተፍ የሚከናወነው የወባ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ አበበ አስታውቀዋል።

በሰቆጣ ወረዳ የማይጉንዶ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አገር ካሳሁን በበኩላቸው እንዳሉት፤ በአካባቢያቸው ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ ቦታዎችን በዘመቻ የማጽዳትና የማዳፈን ሥራ አከናውነዋል።

የጤና ባለሙያዎች በሰጧቸው ምክረ ሃሳብ መሰረት በቤት ውስጥ የአልጋ አጎበር በአግባቡ እየተጠቀሙ መሆናቸውን የተናገሩት ሌላው የቀበሌው ነዋሪ ደግሞ አቶ መሳይ አለነ ናቸው።

በአካባቢያቸው የወባ በሽታን ስርጭት ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ርብርብ ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም