የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፋይናንስን በአንድ ዞናዊ ቋት በማሰባሰብ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለማዳረስ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፋይናንስን በአንድ ዞናዊ ቋት በማሰባሰብ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለማዳረስ ይሰራል
ሮቤ፣ ህዳር 15/2019 (ኢዜአ) የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፋይናንስን በአንድ ዞናዊ ቋት በማሰባሰብ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለማዳረስ ትኩረት መደረጉን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
አገልግሎቱ ከደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር የወረዳዎችን የጤና መድህን አቅም በአንድ ዞናዊ ቋት ለማቀናጀት ያለመ የምክክር መድረክ በባሌ ሮቤ አዘጋጅቷል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጁላ ጉዬ እንዳሉት፣ ባለፉት ዓመታት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል።
ባለፉት ዓመታት በክላስተሩ ሥር በሚገኙ 13 ወረዳዎች የተጀመረውን አገልግሎት በ2018 የበጀት ዓመት ወደ 82 ወረዳዎች በማዳረስ የተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ15 ሚሊዮን በላይ ማድረስ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።
በመረዳዳት መርህ ላይ የተመሠረተውን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዓላማ ለማሳካት የፋይናንስ አቅምን በአንድ ዞናዊ ቋት ማሰባሰብና ማጠናከር ላይ ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል።
ይህም በወረዳዎች ተበታትነው የሚገኘውን የፋይናንስ አቅም በማቀናጀት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉትን የአገልግሎት አሰጣጥ ልምዶች በአንድ ሥርዓት ለማስተሳሰርና ለማህበረሰቡ ወጥ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል አብራርተዋል።
በአገልግሎቱ የታቀፉ ተጠቃሚዎች የጤና አገልግሎትን በቅርበት እንዲያገኙ የተሠራው ሥራ አበረታች ውጤት እያሳየ መምጣቱንም ከተጠቃሚዎች በተገኘ ግብረ መልስ ማረጋገጥ መቻሉን አውስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከዚህ በፊት በተበታተነ መልኩ ሲከናወን የነበረውን የኢንሹራንስ ሥራ በአንድ ቋት ሥር በማቀናጀት ይበልጥ የተሻለና ውጤታማ ለማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
የጤናውን ዘርፍ በአግባቡ በመምራት የአገልግሎቱን ተደራሽነትና ጥራት ለማስጠበቅ የሀብት አስተዳደር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ገመዲ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት በወረዳዎች ደረጃ አንድ የሂሳብ ቋት በማዘጋጀት ጠንካራ የጤና መድህን ሥርዓት ለመገንባት የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም፣ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ባዋቀረው አዲስ የዞን አደረጃጀት መሠረት ሥራውን በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ለመምራት የአንድ ማዕከላዊ ቋት የመመሥረት ሥራ ትኩረት ማግኘቱን አስረድተዋል።
አቶ መሐመድ እንዳሉት፣ በዞኑ በ2019 የበጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል።
የዞናዊ ቋት መተግበሩ ህብረተሰቡን ከመድኃኒት አቅርቦትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚነሱትን ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታ ለመመለስና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ወረዳዎች የተፈጠሩ የሥራ ልምዶችንና አሠራሮችን በአንድ ማዕከል በማቀናጀት የአገልግሎት አሰጣጡን ተመሳሳይነትና ቅልጥፍና ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
የዞናዊ ቋትን ወደ ተግባር ለማስገባት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተካሄደ ያለው የውይይት መድረክ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በውይይት መድረኩ የወረዳ፣ የዞን እና የሻሸመኔ ጤና መድህን ቅርንጫፍ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።