በአማራ ክልል 41 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 41 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ
ባህር ዳር፤ ህዳር 15/2019(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 41 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የግብር ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዘባቸው ጣሴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በ2019 በጀት ዓመት 166 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
እስከ ሕዳር 14 ቀን 2019 ዓም ድረስ በተቀናጀ አግባብ በተደረገ ጥረትም 36 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከመደበኛ ፣ ቀሪው 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ደግሞ ከከተማ የአገልግሎት ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የተሰበሰበው ገቢ ከዓመታዊ ዕቅዱ አንጻር ሲታይ 24 ነጥብ 8 በመቶውን ማሳካት መቻሉን አመልክተው አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ15 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አንስተዋል።
አዲሱን የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አስተዳደር ቴክኖሎጂ በመተግበር የተገኘው ይህ ለውጥ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፤ አዳዲስና የተሻሻሉ አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን የማስፋቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የሕዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ የውጭ እርዳታን ከመጠበቅ ይልቅ፣ የውስጥ ገቢን በፍትሐዊነት መሰብሰብ የህልውና ጉዳይ ሆኖ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በቀጣይም በዕቅድ የተያዘውን ገቢ በተሟላ መንገድ የመሰብሰብ ሥራ ከማስቀጠል ባለፈ የሕግ ተከባሪነትን የማረጋገጥ ተግባር በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በተለይም ከግብር ስወራ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም በሚደረገው ጥረት፣ ኅብረተሰቡ ለገዛው ዕቃ ወይም ላገኘው አገልግሎት ደረሰኝ ጠይቆ በመቀበል የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ከግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ ከቀረቡ 87 ሺህ 903 ቅሬታዎች ውስጥ 97 በመቶ ያህሉ ምላሽ ማግኘታቸውን አመልክተው ከ26 ሺህ 954 የይግባኝ ጥያቄዎች ውስጥ 61 በመቶውን መፍታት መቻሉን አስረድተዋል።
ተቋሙን ከሙስና ለማጽዳት በተወሰደ እርምጃም እስከ ሥራ ስንብት በሚደርስ የዲሲፕሊን ቅጣት እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።