የመደመር መንግሥት በፓናፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኙ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ተደራሽ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት በፓናፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኙ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ተደራሽ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2019 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት በፓናፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኙ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ተደራሽ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገለጹ።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአርክ ውድ ኢንተርቴይመንት ጋር በመተባበር ከህዳር 18 እስከ 19 ቀን በሚካሄደው አህጉራዊ የፊልም ፌስቲቫል ዙሪያ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህ ፌስቲቫል ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ከ500 በላይ የፊልምና ኦዲዮቪዥዋል ባለሙያዎች እንደሚታደሙ ተገልጿል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ፌስቲቫሉን በሚመለከት በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ለፓናፍሪካኒዝም እሳቤ መጎልበት ትልቅ ድርሻ ካበረከቱት ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች ብለዋል፡፡
ኪነ-ጥበብ ሀገራዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ፣ ለማስገንዘብና የጋራ ትርክትን ለመገንባት ጉልህ ሚና እንዳለውም አስገንዝበዋል።
ፌስቲቫሉ አፍሪካውያን የራሳቸውን ታሪክና ሀሳብ በራሳቸው አንደበት እንዲያሰሙ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።
በተለይም በአፍሪካውያን ላይ የተሳሉ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማረምና የአህጉሪቱን እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመደመር መንግሥት በፓናፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኙ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ተደራሽ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በጋራ የተዘጋጀው ይህ ፌስቲቫልም ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኪነ-ጥበብ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ የጎላ ሚና እንዲኖረው ይበልጥ እየተሰራ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።