አየር ኃይል ዘመናዊ ተቋማዊ አቅሙን በመገንባት ዘርፈ ብዙ ድሎችን እያስመዘገበ ነው-የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
አየር ኃይል ዘመናዊ ተቋማዊ አቅሙን በመገንባት ዘርፈ ብዙ ድሎችን እያስመዘገበ ነው-የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
ቢሾፍቱ፣ህዳር 15/2019(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ አየር ኃይል የአገርን ሉዓላዊነትና ደኅንነት የመጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት ከመወጣት ባሻገር በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ለሁለንተናዊ ብልጽግና ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል 91ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደውን የ10 ኪሎ ሜትር ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በመግለጫውም ሁለተኛው የቢሾፍቱ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ኅዳር 20 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አየር ኃይል እንደ አንድ የመከላከያ አካል አገርን በመከላከል፣ በመጠበቅ እና ጠላትን በማጥፋት ድል እያስመዘገበ ቀጣይ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ ግዳጁን እየተወጣ አገርን በማልማት፣ ተቋም በመገንባት እና የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ባለፈው ዓመት የተቋሙን የምሥረታ ቀን አስመልክቶ ለቢሾፍቱ ከተማ እንደ አንድ መለያ (ብራንድ) ተጀምሮ የነበረው የአየር ኃይል ታላቁ የጎዳና ላይ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ በዘንድሮው በዓልም እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በሩጫው ላይ ሠራዊቱ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ እንደሚሳተፉ ጠቁመው፤ መላው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተለያዩ አካባቢዎች ተወጣጥተው በመምጣት አብረው እንዲሮጡ እና በዓሉን በደመቀ ሁኔታ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ሽመልስ ዳዊት በበኩላቸው፤ በውድድሩ ላይ ከ10 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
ከ800 በላይ የሚሆኑ ኢሊት አትሌቶች እንዲሁም በኦሎምፒክ፣ በዓለም ሻምፒዮና እና በጎዳና ላይ ሩጫዎች ተሳትፈው ትልቅ ድል ያስመዘገቡ ታላላቅ አትሌቶች በውድድሩ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የውድድሩን ሽልማት በተመለከተ ሲያብራሩም፤ በሁለቱም ጾታዎች (በወንድም በሴትም) ከ1ኛ እስከ 5ኛ ለሚወጡ አትሌቶች ተመሳሳይ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በሁለቱም ጾታዎች 1ኛ ለሚወጣ አትሌት 500 ሺህ ብር፣ 2ኛ ለሚወጣ 250 ሺህ ብር እንዲሁም 3ኛ ለሚወጣ አትሌት 150 ሺህ ብር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም 1ኛ በመውጣት አሸናፊ የሆኑ አትሌቶችን ላሰለጠኑ አሰልጣኞች ለእያንዳንዳቸው የ100 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።