ቀጥታ፡

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎች በደረቅ ቀናት መሰብሰብ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15 /2019 (ኢዜአ)፦ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎች በደረቅ ቀናት እንዲሰበሰብ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

ኢንስቲትዩቱ  የኖቬምበር 21-30 እና የዲሴምበር 1-10/2026 የአየር ሁኔታ ትንበያና ምክረ ሀሳብ ይፋ አድርጓል።

ባለፉት 10 ቀናት ማለትም ከኖቬምበር 11 እስከ 20/2026 በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብ፣ መካከለኛው፣ ምስራቅና ሰሜን ምስራቅ የተሻለ የደመና ሽፋንና ከመካከለኛ እስከ ከባድ ዝናብ መመዝገቡን ገልጿል።

በተለይ በ23 አካባቢዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚ.ሜ በላይ ዝናብ የተመዘገበ ሲሆን፣ አዶላ (77.6 ሚ.ሜ)፣ ብላቴ (59.4 ሚ.ሜ)፣ ማይጨው (56.8 ሚ.ሜ) እና ያቤሎ (56.7 ሚ.ሜ) ከፍተኛ መጠን ካስመዘገቡት መካከል ይጠቀሳሉ።

ያለፈው የአየር ሁኔታ በግብርናና በውሃ ዘርፎች ላይ ድብልቅ ተጽዕኖ ማሳደሩን ሪፖርቱ አመላክቷል።

እርጥበቱ በደቡብ አጋማሽ፣ በቦረናና ጉጂ ለተዘሩ ሰብሎች፣ ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል እንዲሁም ለጥራጥሬ ሰብሎች መልካም ሁኔታ ቢፈጥርም፣ ሰብል በደረሰባቸው የሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅና መካከለኛው አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ በመጠኑ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

በውሃ ዘርፍም ኦሞ ጊቤ፣ ባሮ አኮቦ፣ ገናሌ ዳዋ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ላይኛውና መካከለኛው አባይ እንዲሁም ላይኛው ተከዜ ተፋሰሶች ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ የገጸ ምድር የውሃ ፍሰት በማግኘታቸው ለውሃ ሀብት ግብዓት አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ከኖቬምበር 21 እስከ 30/2026 በሚኖረው የኖቬምበር ሶስተኛ አስር ቀናት፣ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የቦረና፣ ምስራቅ ቦረና፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ጉጂ፣ ምስራቅ ባሌ፣ ሲዳማ እንዲሁም በሶማሌና ደቡብ ኢትዮጵያ ደቡባዊ ዞኖች የተሻለ ዝናብ እንደሚኖር ትንበያው ያሳያል።

በደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅና ደቡብ ምዕራብ አልፎ አልፎ በ24 ሰዓት ከ11 እስከ 30 ሚ.ሜ ዝናብ ሲጠበቅ፣ በምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ መካከለኛው፣ ምስራቅና ሰሜን ምስራቅ ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ይኖራል።

በተጨማሪም በመካከለኛው፣ ምስራቅና ደቡብ ደጋማ ቦታዎች የሌሊትና የማለዳ ዝቅተኛ ሙቀት አልፎ አልፎ ከ5 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንደሚሆን ተጠቁሟል።

ከዲሴምበር 1 እስከ 10/2026 ባሉት አስር ቀናትም ዝናብ ሰጭ ክስተቶች በበጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት አካባቢዎች እንደሚቀጥሉና በደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅና ደቡብ ምዕራብ አልፎ አልፎ በ24 ሰዓት ከ11 እስከ 29 ሚ.ሜ ዝናብ እንደሚኖር ተመላክቷል።

በሌላ በኩል በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብና ሰሜን ምስራቅ ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል ዝናብ ሲጠበቅ፣ በመካከለኛው፣ ምስራቅና ደቡብ ደጋማ ቦታዎች ዝቅተኛ ሙቀት ከ5 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች በመሆን የሌሊትና የማለዳ ቅዝቃዜ አልፎ አልፎ እንደሚጠናከር የትንበያ መረጃው ያሳያል።

ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ምክረ ሀሳብ፣ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች እርጥበትን በአግባቡ መጠቀም፣ የዝናብ ውሃ ማሰባሰብ፣ የግጦሽ ሳርን መንከባከብ እንዲሁም በደጋማ አካባቢዎች አረም ማስወገድና የጥራጥሬ ሰብሎችን እድገት መከታተል ይገኝበታል።

ወቅቱን ያልጠበቀ እርጥበት በሚጠበቅባቸው ዞኖች የደረሱ የመኸር ሰብሎችን በደረቅ ቀናት በፍጥነት መሰብሰብና መከመር እንዲሁም የዋግ በሽታን ለመከላከል የማሳ ጉብኝት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

በውሃው ዘርፍ ከኖቬምበር 21 እስከ 30/2026 በስምጥ ሸለቆ፣ በኦሞ ጊቤና በላይኛው ባሮ አኮቦ ተፋሰሶች ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የገጸ ምድር ውሃ ፍሰት እንደሚጠበቅ ሪፖርቱ ገልጿል።

በዚህም የግድቦችንና የወንዞችን የውሃ መጠን መከታተል፣ የዝናብ ውሃ ማሰባሰብ፣ የፍሳሽ መውረጃዎችን ማጽዳት እንዲሁም የአፈር መሸርሸር፣ የደለልና የፍሳሽ መውረጃ መዘጋት ስጋቶችን አስቀድሞ መቆጣጠር እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም