የሐረር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከውበት ባለፈ የዜጎችን ኑሮና የንግድ እንቅስቃሴ በቀጥታ የሚያነቃቁ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሐረር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከውበት ባለፈ የዜጎችን ኑሮና የንግድ እንቅስቃሴ በቀጥታ የሚያነቃቁ ናቸው
ሐረር፣ህዳር 15 /2019 ዓ.ም (ኢዜአ)፦ በሐረር ከተማ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከውበት ባለፈ የዜጎችን ኑሮና የንግድ እንቅስቃሴ በቀጥታ የሚያነቃቁ መሆናቸውን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
በመደመር እሳቤ በአገሪቱ የተከናወኑት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተሞች ዘርፈ ብዙ ጸጋዎችን እንዲላበሱ እያስቻሉ ነው።
የሐረር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራዎችም ጥንታዊውን ታሪክና ባህል ከዘመናዊ የከተማ ውበት ጋር በማጣመር ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች አዲስ የዕድገትና የመዝናኛ ምዕራፍ ከፍተዋል።
በተለይም በጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስና ዙሪያው የተከናወኑ ልማቶች ትናንት በቅርሱ ላይ ሊደርስ የነበረውን አደጋ ከመከላከል ባለፈ ጀጎልን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን አስችለዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በከተማዋ የተገነቡት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ ከማድረስ ባለፈ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ያሳደጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ሥራዎች ከውበት ባለፈ የዜጎችን ኑሮና የንግድ እንቅስቃሴ በቀጥታ የሚያነቃቁ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በከተማው በተገነባው ኮሪደር ላይ ፎቶግራፍ በማንሳት የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ዳዊት ተካ፣ በከተማው ቅርስን በመጠበቅና በመንከባከብ ላይ መሠረት ያደረገ የኮሪደር ልማት ሥራ መከናወኑን ተናግሯል።
ከተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ የመጡ ጎብኚዎች ሐረርን እየጎበኙና እርካታቸውን እየገለጹ እንደሚገኙም ጠቁሟል።
የኮሪደር ልማት ሥራው ባስገኘው ትሩፋት በማኅበር ተደራጅተው የፎቶግራፍ ሥራ በማከናወን ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እየጠቀሙ እንደሚገኙም ገልጿል።
የክልሉ መንግሥት የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በስፋት ማከናወኑንና በአሁኑ ወቅትም አጠናክሮ መቀጠሉን ያነሱት ደግሞ በመጽሐፍ ንግድ የተሰማሩት አቶ ደነቀ ብርሃኔ ናቸው።
በተለይ የኮሪደር ልማት ሥራው ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ከተጠቃሚዎቹ አንዱ እርሳቸው መሆናቸውን አንስተዋል።
ከአዲስ አበባ ለጉብኝት ሐረር ከተማ የተገኘችው ወጣት ኒና ተስፋዬ በበኩሏ፣ ባህላዊ ይዘትን መሠረት ባደረገ መልኩ የተገነቡት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ሐረርን እጅግ ውብ እንድትሆን ማስቻላቸውን መመልከቷን ገልጻለች።
አስደማሚ የጅብ ምገባ ትርዒት እንዲሁም የምሽት የሐረር ድባብ ውብ ሆኖ እንዳገኘችው ጠቁማ፣ ይህም ከጠበቀችው በላይ እንደሆነ ተናግራለች።
የከተማው ነዋሪ ወጣት ሁሴን አብደላ እንዳለው ደግሞ የኮሪደር ልማቱ በከተማው መናፈሻዎችን ጨምሮ የተለያዩ መዝናኛ ስፍራዎችን አጎናጽፏል።
በተለይ ጎብኚዎች የሚያርፉባቸውና የሚዝናኑባቸው ስፍራዎች ምቹ በመሆናቸው ሐረርን ተመራጭ መዳረሻ እያደረጓት መሆኑን ተናግሯል።