ቀጥታ፡

የዓዲግራት ከተማን ሁለንተናዊ ልማት ለማሳለጥ የሚያስችሉ መሠረታዊ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ

መቀሌ፤ህዳር 14/2019(ኢዜአ)፦የዓዲግራት ከተማን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ ሁለንተናዊ የልማትና የአገልግሎት እንቅስቃሴዎችን ለማሳለጥ መሠረታዊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የከተማው ባለአደራ አስተዳደር አስታወቀ።

በትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት የባለአደራ አስተዳደር የዓዲግራት ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ፣ አስተዳደሩ ባለፉት 30 ቀናት ባከናወናቸው የሰላምና ፀጥታ ሥራዎችና በተመዘገቡ ለውጦች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አቶ ገብረእግዚአብሔር በቆይታቸው እንዳሉት ሕግን በማስከበር እና ሰላምና ፀጥታን በማስፈን ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

በተለይም ወንጀልን ለመከላከልና ሕግን ለማስከበር በተደረገው ጥረት በስርቆትና በተለያዩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ተሰማርተው የነበሩ ከ120 በላይ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የተጠርጣሪዎች መያዝ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት መሆኑን ጠቁመው፣ የከተማው ነዋሪ ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የአካባቢውን ሰላም በንቃት እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓዲግራት ከተማ ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ከፀጥታ አካላት፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከወጣቶች ጋር ባካሄደው የተቀናጀ ውይይትና የተግባር ሥራ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል።

በኅብረተሰቡና በፀጥታ መዋቅሮች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ወንጀልን አስቀድሞ የመከላከል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አስታውቀዋል።

በከተማው የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በመግታት የነዋሪውን እንቅስቃሴና የንግድ ሥራ አስተማማኝ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አቶ ገብረእግዚአብሔር ጨምረው ተናግረዋል።

በዚህም የከተማውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እና ሁለንተናዊ የልማትና የአገልግሎት እንቅስቃሴዎችን ውጤታማ ለማድረግ የከተማው የባለአደራ አስተዳደር የተለያዩ መሠረታዊ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የከተማውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

የተገኘውን ሰላም አስጠብቆ ለማስቀጠል በኅብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት ትብብር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም