ኖርዌይ የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነትና ዘላቂነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ድጋፍ ታደርጋለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋህር - ኢዜአ አማርኛ
ኖርዌይ የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነትና ዘላቂነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ድጋፍ ታደርጋለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋህር
አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2019 (ኢዜአ)፦ ኖርዌይ የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነትና ዘላቂነት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋህር ገለጹ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ከፍተዋል።
ከዛሬ ሕዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው ጉባዔው “የአፍሪካ የጤና ደህንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነት እና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።
የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋህር በጉባኤው መክፈቻ ላይ ኖርዌይ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በጤና ዘርፍ የረጅም ጊዜ ትብብር እንዳላት ጠቁመው በዚህም የክትባት እና መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ማስፋት መቻሉን ገልጸዋል።
የእናቶችና የሕፃናት ጤናን በዓለም አቀፍ አጀንዳ ደረጃ ከፍ እንዲል ማድረግ መቻሉንና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የአማካይ የሕይወት ዘመን (Life Expectancy) ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
በአፍሪካ ሀገራት መካከል የጤና ሉዓላዊነትን የማጠናከር እና እንደ አፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ያሉ ጠንካራ የአፍሪካ ተቋማትን የመገንባት ተነሳሽነቶች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ወደፊት በመራመድ የሉሳካ አጀንዳ መርህን ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባ ገልጸው ይህም ለወደፊቱ አጋርነትን መገንባት፣ በሀገራት የሚመራ ልማትን ማበረታታትና የሀገር ውስጥ የገንዘብ አቅምን ማሰባሰብ ማለት መሆኑን ጠቁመዋል።
ኖርዌይ ዓለም አቀፍ የጤና ዝግጁነትንና ፍትሐዊነትን ለማራመድ ቁርጠኛ ሆና እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
ይህ ሥራ ጠንካራ እና ጽኑ የሆኑ ብሔራዊ የጤና ሥርዓቶችን በመገንባት እንደሚጀምር ገልጸው በእነዚህ ጥረቶች ውስጥ ኖርዌይ ንቁ አጋር እንደምትሆን ገልጸዋል።
የሩሲያ ፌዴሬሽን የመንግሥት ፀሐፊ እና ምክትል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ኦሌግ ኦሌጎቪች ሳላጋይ በዚሁ ወቅት፤ ጉባኤው በአፍሪካ ሀገሮች በሕዝብ ጤና ዘርፍ እውነተኛ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ከሚያስችሉ እጅግ አስፈላጊ ጉዳዮች አንዱ ነው ብለዋል።
ይህም የሕክምና አገልግሎቶችንና የንፅህና መሠረተ ልማቶችን ማሳደግ፣ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ ማዋልን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚያካትት ተናግረዋል።
የሩሲያ ፌዴሬሽን የሕዝብን ጤና በመጠበቅ በኩል ለአፍሪካ አጋሮቿ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ጠቁመው፤ በቅርቡ የተካሄደው ሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ በዘርፉ ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማስፋፋት ትልቅ እድል መፍጠሩን አንስተዋል።
በተለይም ወረርሽኝ፣ በሽታዎችን በመከላከልና በመታገል በኩል በጣም ቅርብ የሆነ ትብብር መመስረቱን ጠቁመዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ መሪዎች ለአህጉሪቱ የጤና ደኅንነት ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ገልጸዋል።
እነዚህን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ወደ ተግባር ለመቀየር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነን ብለዋል።
እ.ኤ.አ. በ2017 የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በአፍሪካ አህጉር ሞቃታማ አካባቢዎች ተላላፊ በሽታዎችን ለማጥፋት የሚያስችለውን 'Reaching the Last Mile Fund' የተሰኘ ፈንድ ማቋቋማቸውን አስታውቀዋል።
እነዚህ በሽታዎች መከላከል የሚቻል የዓይን መታወርንና ዘላቂ የአካል ጉዳትን እያስከተሉ እንደነበር ገልጸው ማንኛውም ግለሰብ መከላከል በሚቻል በሽታ እንዳይሰቃይ የሚያስችል ተልዕኮን በመደገፍ አጋር መሆናችን ያስደስተናል ነው ያሉት።
የአንድ ሕፃን መወለድ የደስታ ቀን መሆን እንዳለበት ገልጸው እያንዳንዷ እናት እሷም ሆነች ልጇ የሚያስፈልጋቸውን የጤና ክብካቤ እንደሚያገኙ ማረጋገጥ የሁሉም የጋራ ሀላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት እንዲያግዝ እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2025 የመሐመድ ቢን ዛይድ የሰብዓዊነት ፋውንዴሽንና ሌሎች መሥራች ለጋሾች በአቡ ዳቢ ከአፍሪካ የጤና ሚኒስትሮች ጋር በመሰባሰብ 'The Beginning Fund' የተሰኘውን ፈንድ ለማስጀመር መወሰኑን አስታውሰዋል።
ይህ ፈንድ፣ በአፍሪካ ሀገራት የእናቶችንና የአራስ ሕፃናትን ጤንነት ለመጠበቅ በተረጋገጡ ውጤታማ የጤና ጣልቃ ገብነቶች ላይ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።