ቀጥታ፡

በመቀሌ ከተማ ሰላምን የማጠናከርና ገበያን የማረጋጋት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው -ነዋሪዎች

መቀሌ፤ ህዳር 14/2019 (ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልል የፌደራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር  በመቐለ ከተማ  እያከናወናቸው ያሉ ሰላምን የማጠናከርና የገበያ ማረጋጋት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።

ባለአደራ አስተዳደሩ በከተማው በሰላም ማጠናከር  እንዲሁም  በመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትና በገበያ ዋጋ ማረጋጋት እየሰራቸው ባሉ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል ።                                                                                                                                                በመቐለ ከተማ ዓዲ ሐቂ ገበያ ማዕከል በንግድ ስራ የሚተዳደሩ ወይዘሮ ጊደና ብርሃነ እንደገለጹት፣ በከተማው የመሠረታዊ ሸቀጦችና ምርት  አቅርቦት እንዲሁም  ዋጋ መሻሻል አሳይቷል። 

ከዚህ ቀደም የነበረውን የሰላም እጦት ተከትሎ እስከ አንድ ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ዛላ   በርበሬ አሁን ላይ ወደ 650 ብር ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል።                                                                              

በተመሳሳይ የአምስት ሊትር የምግብ ዘይት ዋጋ ከ2 ሺህ150 ብር ወደ አንድ ሺህ 900 ብር ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል።

ሌላዋ ነጋዴ ወይዘሮ ጠዓሞት አብርሃ በበኩላቸው፣ በገበያ መረጋጋት ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የዳቦ ዱቄት፣ ስኳርና ሌሎች ምግብ ነክ መሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ቅናሽ እየታየ መሆኑን ጠቁመው ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመግታት የሚደረግ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል ።

በአሁኑ ወቅት በገባያ ላይ የመሰረታዊ ሸቀጦች የአቅርቦት እጥረት እንደሌለ ጠቁመዋል።

የከተማው ነዋሪና የመንግስት ሠራተኛ ወይዘሮ ልዋም ግደይ  በበኩላቸው ባለአደራ አስተዳደሩ በሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ህግን በማስከበር የጀመራቸው ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውንና ይበልጥ መጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል። 

በተለይም በገበያ መረጋጋት ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጭ  መሆኑን ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ ከባለአደራ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት መሥራቱም ዘላቂ ሰላምና የኑሮ መረጋጋትን ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የትግራይ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ባልደረባ ወጣት ተወልደ ገብረሚካኤል በበኩሉ፣ ባለአደራ አስተዳደሩ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የህዝቡን  ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ተስፋ ሰጭ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግሯል ።

በጸጥታና ሰላም ማጠናከር በሚያከናውናቸው ተግባራት አበረታች ለውጦች መታየታቸውን ጠቁሞ የደመወዝ ክፍያ መጀመሩም ተስፋ ሰጭ ተግባር መሆኑን ገልጿል ።

በተለይም ሰላም ለማጽናት በሚከናወኑ ተግባራት ሁሉም አካላት ከአስተዳደሩ ጎን ሊቆም እንደሚገባ አመልክቷል።

በሰላምና ፀጥታ፣ በህግ ማስከበርና ገበያን በማረጋጋት ረገድ የህዝብን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ በባለአደራ አስተዳደሩ  የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሹሻይ አማረ (ዶ/ር) ናቸው።

በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ ስራዎች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአስተዳደሩን  የአንድ ወር የስራ አፈፃፀም በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ማንሳታቸው ይታወሳል።


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም