ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ለማከናወን ተችሏል- የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር

ጎንደር፣ህዳር 14/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት እሳቤ በኢትዮጵያ ዘላቂ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወን ማስቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ ገለጹ።

የመደመር መንግሥት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ያስቀመጠው አቅጣጫ ቴክኖሎጂን እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ዕድገት መሣሪያ፣የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ እና የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ማቅለያ አድርጎ በማየት ላይ የተመሠረተ ነው።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር የተሰጥኦ ማበልጸጊያ፣ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ልማት መድረክ ዛሬ አካሂዷል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዳንኤል ጉታ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ዘላቂ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ኢትዮጵያ "ዲጂታል 2030" ራዕይን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ታላላቅ መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋትና የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን የመከላከል ሥራ እያከናወነች መሆኗን አመልክተዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ በተቋማት ላይ የተፈጸሙ ከ71 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን በብቃት ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል።

በዘርፉ የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ብሔራዊ ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች በትብብር እየሠሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በጋራ ምርምር ዘርፍም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል በመጠቀም፤ በአማርኛ፣በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ጥቃቶችንና የሐሰት መረጃዎችን የሚለዩ ሀገር በቀል ሞዴሎችን ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የኮምፒውቲንግ እና አናሊቲክስ ማዕከል ዳይሬክተር ሰብለ ኃይሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የዲጂታል 2030 ራዕይን እውን ለማድረግ በጠንካራ ቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በውጭ አቅም ላይ ብቻ ጥገኛ ሳይሆኑ ዘላቂ ሀገራዊ ልማትን ለማምጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በተግባራዊ ፕሮጀክቶች በማሳተፍ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ካሳሁን ተገኝ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የሳይበር ደኅንነት እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ለብሔራዊ ደኅንነትና ለዲጂታል ኢኮኖሚ መሠረት ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ትኩረቱ በሚያስመርቃቸው ተማሪዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ የሚሠለጥነው የሰው ኃይል ለሀገር ችግር መፍትሔ የማበርከት አቅምና ምርምሮች ወደ ተግባራዊ ለውጥና ፈጠራ መቀየራቸው ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ የምትፈልገው ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂን የሚፈጥር፣የሚመራና ለማኅበረሰቡ ጥቅም የሚያውል ትውልድ መሆኑንም አመልክተዋል።

በመድረኩ ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም