ቀጥታ፡

አፍሪካ የጤና ሉዓላዊነቷን በማረጋገጥ ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅ አለባት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2019 (ኢዜአ)፦ አፍሪካ የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በመድኃኒትና ክትባት ምርት፣ በጤና ፋይናንስ፣ በምርምርና በወረርሽኝ ዝግጁነት ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለባት የብሩንዲ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ-መንበር ኤቫሪስት ንዳይሺሚዬ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ከፍተዋል።

“የአፍሪካ የጤና ደህንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነት እና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሃሳብ የሚቆየው ጉባኤም ከዛሬ ሕዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል።

የብሩንዲ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ኤቫሪስት ንዳይሺሚዬ በጉባኤ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኮቪድ-19፣ ኤምፖክስ፣ ኮሌራ፣ ኢቦላና ሌሎች ወረርሽኞች አፍሪካ በውጭ ሀገራት በሚመረቱ ክትባቶችና መድኃኒቶች ላይ ያላትን ጥገኝነት በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

አፍሪካ የጤና ሥርዓቷን በራሷ ሀብትና አቅም ለማጠናከር በብሔራዊ በጀት ለጤና የሚመደበውን ድርሻ ማሳደግ፣ የአፍሪካ መድኃኒትና ክትባት ምርትን ማስፋፋት፣ የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠንና ማቆየት እንዲሁም የምርምርና የመረጃ አቅሟን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይም ከ20 ዓመታት በፊት በአቡጃ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሀገራት ከብሔራዊ በጀታቸው ቢያንስ 15 በመቶውን ለጤና ለመመደብ የገቡትን ቃል በተግባር ማሳካት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የጤና ምርቶችን በራሳቸው አቅም ማምረት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን በመጠቀም የጤና ምርቶች የጋራ ገበያ መፍጠርና የወረርሽኝ ምላሽ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባም አክለዋል።

በብሩንዲ የልማት ርዕይ 2040 እና 2060 መሰረት ጤናን የልማት ማዕከል በማድረግ፣ በማኅበረሰብ ደረጃ የሚሰጥ የጤና አገልግሎትን፣ የክትባትና የበሽታ መከላከል ሥራዎችን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

በተጨማሪም 2026 የውሃና የንጽህና ዓመት መደረጉን በማንሳት ንጹህ ውሃና ተገቢ የንጽህና አገልግሎት ለሕዝብ ጤና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልም የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 የምትመኘው አፍሪካ ጤናማ ሕዝብ ያላት፣ ዜጎቿን የምትጠብቅና የራሷን መፍትሔዎች የምታመርት አህጉር እንድትሆን የጋራ ቁርጠኝነትና ተግባራዊ እርምጃ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም