አፍሪካ በምርት አቅርቦት ዘርፍ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንድትሆን እሴት የመጨመር ሥራዎችን ማሳደግ ይገባታል - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ በምርት አቅርቦት ዘርፍ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንድትሆን እሴት የመጨመር ሥራዎችን ማሳደግ ይገባታል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 14 /2019 (ኢዜአ)፦ አፍሪካ በምርት አቅርቦት ዘርፍ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንድትሆን እሴት የመጨመር ሥራዎችን ማሳደግ እንደሚገባት የትሬድማርክ አፍሪካ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አስገነዘቡ።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ትሬድማርክ አፍሪካ በጋራ የተዘጋጀው የአፍሪካ ንግድ ልማት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፎረሙ እንደገለጹት፤ አፍሪካ ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ ወደ ውጭ በመላክ ውጤታማ ልትሆን አትችልም።
ከአፍሪካ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች እሴት የተጨመረባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ አመልክተው፤ ሀገራት ይህንን ማጠናከር የሚያስችላቸውን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል።
የአፍሪካ የወደፊት የኢኮኖሚ ዕጣ ፈንታ መገንባት ያለበት በጠንካራ የማምረት አቅም፣ በላቀ እሴት መጨመርና ይበልጥ ተወዳዳሪ በሆኑ ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶች ላይ በመመሥረት መሆኑንም ገልጸዋል።
በንግድ ዘርፍ አህጉራዊ ትስስሮችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስታውሰው፤ ለዚህም የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና የሚያመጣቸውን ዕድሎች በአግባቡ መጠቀም አለብን ነው ያሉት።
የንግድ ድርጅቶችም ቀጣይነት ባለው መልኩ ምርትን ማቅረብ፣ መስፈርቶችን ማሟላት፣ ተአማኒነት ያላቸውን ማረጋገጫዎች ማግኘት እና በተወዳዳሪ ዋጋ ማቅረብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ውጤታማ የንግድ ትስስር ለመፍጠር የአቅራቢዎችን ችግር የሚፈታና ልውውጡን የሚያሳልጥ ሥርዓት መዘርጋት ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
የትሬድማርክ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴቪድ ቢር በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ጥራት ላይ መሥራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም አስተማማኝ የምርት ፍተሻ ሥርዓት፣ አክሪዲቴሽንና ዕውቅና አሰጣጥ ላይ የበለጠ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።
አዳዲስ የኤሌክትሮኒክስ የጭነት መከታተያ ሥርዓቶች፣ እርስ በእርስ ተናበው የሚሠሩ የጉምሩክ አስተዳደር ሥርዓቶችን ጨምሮ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን መጠቀም ዘመኑ የሚጠይቀው አካሄድ ነው ብለዋል።
ትሬድማርክ አፍሪካ ከ100 በላይ የዲጂታል የንግድ ሥርዓቶች እንዲዘረጉ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ በዚህም ለውጦችን ተመልክተናል ነው ያሉት።