ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሀገር ውስጥ ምርትና የጤና ሥርዓቱን በማጠናከር ላይ ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14 /2019 (ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሀገር ውስጥ ምርትና የጤና ሥርዓቱን በማጠናከር ላይ እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
  
5
ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።
 

ከ100 በላይ ከሆኑ ሀገራት የተውጣጡ ከ30,000 በላይ ተሳታፊዎች በዚህ ታላቅ አህጉራዊ መድረክ ላይ ታድመዋል።
  
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የጤና ደኅንነትና ሉዓላዊነት የአስተዳደርና የኢንቨስትመንት ማዕከል ሊሆኑ እንደሚገባ  ገልጸዋል።
  

ሕይወትን ለመታደግ በመደበኛ ጊዜም ሆነ በቀውስ ወቅት አስተማማኝ የጤና ሥርዓት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው፣ ከሕክምና በፊት ንጹሕ ውኃ፣ የተመጣጠነ ምግብ እና አስተማማኝ የሕፃናት ማሳደጊያ አካባቢ መኖር  የጤና ኃላፊነት መሠረቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
  

ኢትዮጵያ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በቀጥታ ወደ ቤተሰቦች ለማቅረብ የምትጠቀምበት የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር የሥርዓቱ ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን ነው የገለጹት።
 

በመላ ሀገሪቱ ማኅበረሰቦችን በማገልገል ላይ ከሚገኙት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አገልግሎታቸው በማኅበረሰብ እምነት ላይ የተገነባ፣ የጤና ስጋቶችን የሚለይና ቤተሰቦች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከሕመም ጋር ተያይዞ ቤተሰቦች ላይ የሚደርሰውን የገንዘብ ጫና ለመቀነስ የጤና መድን አገልግሎት እየተስፋፋ መሆኑን ነው ያስረዱት።
  

ይህ እርምጃ እያንዳንዱ ቤተሰብ በጋራ ድጋፍ እንዲተማመን የሚያስችል የባህል እሴት መገለጫ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጥበቃው ትርጉም እንዲኖረው የጤና ተቋማት በቂ ባለሙያ፣ መድኃኒት፣ በሽታን የሚለዩ ላቦራቶሪዎች እና ተገቢ ግብዓቶች ሊሟሉላቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።
  
 
አስፈላጊ መድኃኒቶችን በጥራትና በደኅንነት ደረጃ በስፋት ለማምረት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ባለፈው ዓመት ለመድኃኒቶችና ለሚገቡ ክትባቶች የዓለም ጤና ድርጅት የብቃት ደረጃ 3 መሰጠቱን አስታውሰዋል።
  

ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾች ኢትዮጵያንና ቀጣናውን በላቀ ደረጃ እንዲያገለግሉ ጠንካራ መሠረት እንደጣለ አስረድተዋል።
  

በተጨማሪም የጤና ደኅንነትን ከኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማቆራኘት፣ የኢንቨስትመንትና የምርት መስፋፋትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ ቀጣናዊ ፍላጎት ወሳኝ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
 

በአዲስ አበባ ለተሰበሰቡ ኃላፊዎች ቀጣይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሶስት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች አስቀምጠዋል።
  

እነዚህም የሕክምና ልህቀት ማዕከላትን ማልማት፣ የአፍሪካ የጤና ምርቶች አስተማማኝ ገበያ ለመፍጠር በጋራ መግዛት እና ለቃል ኪዳኖች ተጠያቂነትን በማስፈን የሚመለከተውን አካል ፣ የፋይናንስ ምንጩንና የግምገማ ጊዜውን ግልጽ ማድረግ የሚሉ ናቸው።
  

የአየር ንብረት ለውጥ የዝናብ እና የሙቀት መጠንን በመቀየር በሽታዎች የሚስፋፉባቸውን ሁኔታዎች እንደሚነካ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎች የሚያስከትሉትን የጤና ስጋትም አንስተዋል።
  

ጤናንና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የተያያዙ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰው የሕክምና ቀጣይነትና የሀገር ውስጥ አቅም መገንባት  ለሕዝብ አመኔታ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
  

የስኬት መለኪያው በቃል ኪዳን ብቻ ሳይሆን ዜጎች በሚያገኙት የሕክምና አገልግሎት ጥራት፣ አስተማማኝነት እና ተደራሽነት ላይ በሚታይ ተጨባጭ መሻሻል መሆን እንደሚገባው  አጽንዖት ሰጥተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም