ቀጥታ፡

መደመር በአፍሪካ የጤና ትብብር ውስጥ እንደ መሪ ፍልስፍና ሊያገለግል ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2019 (ኢዜአ)፦ መደመር በአፍሪካ የጤና ትብበር ውስጥ እንደ መሪ ፍልስፍና ሊያገለግል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።

ከ100 በላይ ከሆኑ ሀገራት የተውጣጡ ከ30,000 በላይ ተሳታፊዎች በዚህ ታላቅ አህጉራዊ መድረክ ላይ ታድመዋል።

በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ፤ "የአፍሪካ የጤና ደህንነት እና ሉዓላዊነት: ከጤና ጥገኝነት እና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና የማይበገር አቅም መሸጋገር" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ሰው ሰራሽ አስተውሎትንና ዲጂታል ጤናን የአፍሪካ የዲፕሎማሲ እና የልማት አጀንዳ ማዕከል መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት በሰው ሰራሽ አስተውሎትና ዲጂታል ጤና ሻምፒዮን የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲጂታል ለውጥ በአፍሪካዊ ምርምር፣ በቀጣናዊ የሕክምና እውነታዎች እና በሉዓላዊ የመረጃ አስተዳደር ላይ መመሥረት እንዳለበት አመልክተዋል።

ቴክኖሎጂን በዕለት ተዕለት የሕክምና አገልግሎት ውስጥ ለማካተት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መመሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

ዲጂታል መሣሪያዎች በተግባር ውጤታማ እንዲሆኑ የአፍሪካ ተመራማሪዎችና የጤና ባለሙያዎች የአገር ውስጥ ሁኔታን፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋን እና የጤና ባለሙያዎች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊቀርጿቸውና ሊፈትሿቸው እንደሚገባም ነው ያስረዱት።

ይህንን እውን ለማድረግ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ቀጣይነት ያለው የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም የጤና መረጃዎችን ለመጠበቅና ድንበር ተሻጋሪ የእውቀት ልውውጥን ደኅንነቱን በጠበቀ መልኩ ለማካሄድ አፍሪካውያን ራሳቸው የሚያወጧቸው ደንቦች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።

የተቋማት አቅም ግንባታና የባለሙያዎች ተጠቃሚነት የንግግሩ ሌላኛው ትኩረት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት ከአፍሪካ የጤና ተቋማት ጋር የጋራ ምርምር ማካሄድ እንደሚችልና በግንባታ ላይ ያለው የመደመር ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ከመላ አፍሪካ ተማሪዎችን በመቀበል የላቀ ስልጠናና ምርምርን ለማስፋት እንደሚሰራ ነው ያብራሩት።

ግኝቶታቸው አፍሪካን የሚጠቅሙና ዓለም አቀፍ እውቀትን የሚያሳድጉ በመሆናቸው፣ ወጣት ተመራማሪዎች ላቦራቶሪዎች፣ የምርምር የገንዘብ ድጋፍ እና የሥራ ዕድሎች እንደሚያስፈልጓቸው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን የአስተዳደር ፍልስፍና መደመርን በመጥቀስ ተቋማት የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረታቸውን እንዲያቀናጁ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ መርህ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ሊተገብር ይገባል ብለዋል።

በአንድ ሀገር ያለ ላቦራቶሪ ሌሎች ሀገራት አዲስ በሽታ እንዲለዩ እና በሌላ ሀገር ያለ አምራች ለቀጣናው የጤና አገልግሎት ማቅረብ እንደሚችል በማንሳት፣ የቀጣናው ትስስር የጋራ ጥንካሬ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት ኮፕ32ን በአዲስ አበባ እንደምታስተናግድ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአየር ንብረት ውሳኔዎች በማስረጃና በልምድ እንዲደገፉ አጋሮች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም