ቀጥታ፡

አፍሪካ በዓለም አቀፍ የንግድ መድረኮች በአንድ ድምፅ በመቆም የሕግ አውጪነት ሚና ልትጫወት ይገባል - የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2019 (ኢዜአ)፦ አፍሪካ በዓለም ንግድ ድርጅት እና መሰል መድረኮች በአንድ ድምፅ በመቆም የሕግ አውጪነት ሚና ልትጫወት እንደሚገባት የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

የአፍሪካን የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት በምርት ጥራት ለማሳደግ ያለመው የ2026 የአፍሪካ ንግድ ልማት ፎረም በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የትሬድማርክ አፍሪካ የቦርድ ሰብሳቢ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ፣ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የፓን-አፍሪካኒዝም መገኛ የሆነችው አዲስ አበባ የአህጉሪቷን ቀጣይ የታሪክ ምዕራፍ ለመቅረጽ የሚደረገውን ውይይት ማስተናገዷ ተገቢ ነው።

አፍሪካ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ፣ ሰፊ መሬት፣ ማዕድናትና እያደገ ያለ ገበያ እንዳላት አስታውሰው፤ ሆኖም እሴት የመፍጠር እና ሀብትን በሀገር ውስጥ የማስቀረት ልማድ ባለመዳበሩ ለዘመናት ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ በመላክ ትርፉን ለሌሎች ስታስረክብ መቆየቷን አንስተዋል።

የስኬት መለኪያው ወደ ውጭ በሚላከው የጥሬ ዕቃ መጠን ሳይሆን በሚፈጠረው እሴትና የሀገርን ጥቅም በማረጋገጥ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በወረቀት ላይ ብቻ ሳይቀር በአፍሪካውያን መካከል ያለውን ንግድ ለማሳደግ፣ ፋብሪካዎችን ለማጠናከርና የሥራ ዕድል ለመፍጠር መዋል እንዳለበትም ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ ከለላ እየጨመረ በመምጣቱና ወደ ገበያ የመግባት ዕድል በምርት ደረጃዎችና በብቃት ማረጋገጫ የሚወሰን መሆኑን ጠቅሰው፤ አፍሪካ በዓለም ንግድ ድርጅት እና መሰል መድረኮች በአንድ ድምፅ በመቆም የሕግ አውጪነት ሚና ልትጫወት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጥራት የንግድ መገበያያ ገንዘብ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የጥራት ተቋሞቿን በአንድ ጣሪያ ሥር በማሰባሰብ በኢትዮጵያ የተመረተ የሚለው ስያሜ ተዓማኒነት እንዲኖረው እየሠራች መሆኗን ጠቁመዋል።

ሀገሪቷ ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የምታደርገው ጉዞም ለኢኮኖሚ ማሻሻያዎቿ ሕጋዊ ዋስትና እንደሚሰጥና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምትገነባው የመሠረተ ልማት ትስስር ለጋራ ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

አፍሪካውያን በዚህ ፎረም የጥራት መሠረተ ልማት ግንባታ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ፣ በሎጂስቲክስ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እና ሁሉን አቀፍ አጋርነት መፍጠር ላይ ትኩረት ሊያደርጉባቸው ይገባል ብለዋል።

የተናጠል አቅሞችን በጋራ ዓላማ ዙሪያ በማሰባሰብ የላቀ ውጤት ማምጣት የሚያስችለውን የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የመደመር ፍልስፍና ለአፍሪካውያን በማቅረብ፣ በአፍሪካ የተመረተ የሚለው ስያሜ የልህቀትና የተዓማኒነት መገለጫ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም